
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥቷል።
የካቲት 23 የሚከበረውና የጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው የዓድዋ ድል በዓል በመጪው ቅዳሜ በድምቀት እንደሚከበር ነው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የገለጸው።
በባለፈው ዓመት ከተከበረው 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል የተገኙ በርካታ ልምዶችን በመውሰድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና ተቋማትን በማስተባበር በዓድዋ ድል ቀን የዓድዋ ጀግኖችን ለመዘከር ቀደም ብሎ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን መግለጫውን የሰጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገልጸዋል።
ዝግጅቱን በበላይነት የሚያስተባብረውና የሚመራው የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዕለቱ የሠራዊቱን ጀግንነትና መስዋዕትነት በሚያጎላ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁንና ለዚህም የተዘጋጁ በርካታ ዝግጅቶች፤ የተለያዩ ጥበባዊ ክዋኔዎችና ታሪካዊ ትዕይንቶች እንደሚኖሩም አብራርተዋል።
ዕለቱ የዓድዋ ጀግኖች አርበኞች ህይወታቸውን መስዋዕት ማድረጋቸው የአሁኑ ትውልድ የሀገር ፍቅርንና ክብርን የሚማርበት ነው ብለዋል። በዓሉ የዓድዋ ጀግኖችን ለመዘከር ታስቦ በተገነባው የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚዬም እንደሚከበርም ተገልጿል።
ዘጋቢ:–ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!