
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መጻሕፍት በወቅቱ ታትመው ባለመቅረባቸው በትምህርት ጥራት ላይ ሌላ ፈተና መፈጠሩን መምህራን እና የትምህርት ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የመጻሕፍት አቅርቦት ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል። መማሪያ መጻሕፍት በወቅቱ ተሟልተው ባለመቅረባቸው በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን በጃናሞራ ወረዳ ያነጋገርናቸው የትምህርት ባለሙያዎች ነግረውናል።
ከአስሩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሚማሩባቸው የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ሦስቱ ታትመው ባለመቅረባቸው አሁንም ድረስ ትምህርት አለመሰጠቱን ነው በጃናሞራ ወረዳ አሁጫራ ቀበሌ የአረባይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ተመስገን ተካ የነገሩን።
ርዕሰ መምህሩ እንዳሉት በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ፈተና ቢኾንም የመማሪያ እና ማስተማሪያ መጻሕፍት ተሟልተው አለመቅረብም በትምህርት ሥራው ላይ ሌላ ችግር ፈጥሯል። እስከ አሁንም “ከአስሩ የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ሰባቱን የትምህርት ዓይነቶች ብቻ ነው ተማሪዎች እየተማሩ የሚገኙት” ብለዋል፡፡
ባለሙያው እንዳሉት የግብረ ገብ፣ ሙያ እና ቴክኒክ እና አይሲቲ የትምህርት ዓይነቶች መጻሕፍት ታትመው ባለመቅረባቸውን እና እነዚህን ትምህርት ዓይነቶች የሚያስተምሩ መምህራን አለመመደባውንም ገልጸዋል። በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ሕትመቱ መድረስ እና መምህራን ተመድበው ማስተማር ካልተቻለ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሌላ ችግር እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የጃናሞራ ወረዳ ትምሕርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀብታሙ ኃይሉ በወረዳው በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መቅረብ ከነበረበት አሥር የትምህርት ዓይነቶች መጻሐፍት ውስጥ የግብረ ገብ፣ ቴክኒክ እና ሙያ እና አይሲቲ የትምህርት አይነቶች እንዲኹም ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ የአማርኛ መማሪያ መጽሐፍ ታትሞ አለመድረሱንም ገልጸዋል፡፡
ለቴክኒክ እና ሙያ እንዲኹም ለአይሲቲ የትምህርት ዓይነት መምህር ያልተመደበላቸው ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ኀላፊው ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በቀጣይ ተማሪዎችን ለመመዘን ፈተና እንደኾነባቸው ነው የገለጹት። ችግሩን ለትምህርት ቢሮ ቢያቀርቡም አሁንም ድረስ መፍትሄ አለመገኘቱን ነግረውናል።
የአማራ ክልል ትምህርትን ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር ካሴ አባተ መምህራንን ማሟላት የወረዳዎች ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል። በእጥረት የተነሱት የአንደኛ ደረጃ መማሪያ መጽሐፍት በአንድ ለአራት ሂሳብ ታትመው በየክዘና ማዕከላት ከገቡ መቆየታቸውን ገልጸዋል። የመማሪያ መጽሐፍቱ እስከ አሁን ወደ ትምህርት ቤቶች ያልተሰራጨበትን ምክንያት ቢሮው እንደሚያጣራም ገልጸዋል።
የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሐፍ መታተሙን ገልጸው በትራንስፖርት ችግር ወደ ትምህርት ቤቶች አለመሰራጨቱን ገልጸዋል። በቅርቡም ተደራሽ ይኾናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!