
ሕጉስ ስለንግዱ ሥነ ምግባር ምን ይላል?
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ንግድን በሥራ መሥክነቱ የመረጠ አካል ትርፍ በማግኘት የግል ጥቅሙን ወደ ተሻለ ደረጃ የማሸጋገር ፍላጎት አለው። ነግዶ የማትረፍ ወይም ጥቅም የማግኘት መብት እና ነጻነትም አለው።
ነጋዴው በጥራቱ እና በመጠኑ ደረጃውን የጠበቀ፣ በተፈለገው ቀን እና ቦታ የተፈለገውን አገልግሎት የመሥጠት ግዴታን መወጣት አለበት።
ሸማቹም የሚፈልገውን ነገር በተመጣጣኝ ዋጋ እና በተገቢው ጥራት ማግኘት መብት አለው። ለተሰጠው አገልግሎት ደግሞ የገበያ ሕግ በሚያዘው መሠረት ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለበት። በነጋዴው እና ሸማቹ መብት እና ግዴታ መካከል እንዲኖር የሚፈለገው ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ ግንኙነት ነው።
የንግድ እንቅስቃሴ የሻጭ እና የሸማች ወገኖች ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የአጠቃላይ ኅብረተሰብ እድገት ጉዳይም በመኾኑ ከማጭበርበር፣ ከማታለል እና ከሸፍጥ የጸዳ መኾን አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ዘርፉን በግብረ ገባዊ ሕግጋት እና በሥነ ምግባራዊ ደንቦች ጭምር መጠበቅ እንደሚገባ ጠና ደዎ (ዶ.ር) ሰው፣ ግብረ ገብ እና ሥነ ምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ አስቀምጠውታል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ውድድር ሸማቾች ጥበቃ እና መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎች አቅርቦት ክትትል ጉዳይ ዳይሬክተር ታፈረ ይመር እንዳሉት ንግድ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከናወን ለማስቻል የራሱ ሕጎች ወጥተውለታል። ከእነዚህ ሕጎች ውስጥ ደግሞ የሸማቹን ማኅበረሰብ መብት እና ጥቅም ለማስከበር የወጣው አዋጅ ቁጥር 813/2006 በዋናነት ይጠቀሳል።
አዋጁ በዋናነት ከንግድ ውድድር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን በተለይም የሸማቹን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የወጣ አዋጅ ነው። አዋጁ በርካታ ዝርዝር ነገሮችን ያካተተ ቢኾንም ለዛሬ ከሸማቹ አኳያ የተቀመጡ ነጥቦችን እናንሳ።
አዋጁ የንግዱ ማኅበረሰብን ተገቢ ካልኾነ የገበያ ተግባራት የሚከላከል እና ለነጻ ገበያ ውድድር አመችነት ያለው ሥርዓትን ለማስፈን፣ ሸማቾች ለደኅንነታቸው እና ለጤንነታቸው ተስማሚ የኾነ ነው። ላወጡት ዋጋም ተመጣጣኝ የኾነ የንግድ ዕቃዎችን እና አግልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱን ማረጋገጥ እና ምጣኔ ሃብታዊ ልማትን ለማፋጠን ዓላማዎችን መሠረት ያደረገ ነው።
የሸማቾች መብት ምንድን ነው?
ሸማቾች ለሚገዙት ምርት ወይንም የአገልግሎት ጥራት እና ዓይነት በቂ፣ ትክክለኛነት፣ የፈለጉትን እቃ ወይም አገልግሎት አማርጦ የመግዛት መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል። የእቃዎችን ወይም የአገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየታቸው፣ በማማረጣቸው ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጋቸው እንዲገዙ አይገደዱም።
በማንኛውም ነጋዴ በትህትና እና በአክብሮት የመስተናገድ እንዲሁም በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ መብት አላቸው።
የንግድ እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመጠቀማቸው ምክንያት ለደረሰባቸው ጉዳት አምራቾች፣ አስመጭዎች፣ ጅምለኞች ወይም ቸርቻሪዎች በተናጠል ወይም በቡድን ተጎጅውን የመካስ ግዴታ አለባቸው።
ለምሳሌ አንዲት ሴት ደረጃውን ያልጠበቀ ቅባት ተጠቅማ ሰውነቷ ላይ ጉዳት ቢደርስባት አምራቹ ወይም አስመጭው ወይም ጅምላ አከፋፋይዩ ወይም ቸርቻሪው በጋራ ወይም በተናጠል የመካስ ግዴታ አለባቸው። የካሳው ጉዳይም በፍርድ ቤት የሚዳኝ ይኾናል ይላል።
ሸማቾች የዋጋ ዝርዝር የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው። ነጋዴውም የንግድ እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ ላይ በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እንዳለበት ያስቀምጣል። ዋጋም የታክስ እና የሌሎችን ሕጋዊ ክፍያዎችን ያካተት መኾን አለበት።
በአንድ የንግድ እቃ ሥም ላይ የተሠራበት ሀገር፣ ክብደት፣ መጠን፣ ጥራት፣ አጠቃቀም፣ ባህርይ፣ ጥቅም እና ጉዳት የመሳሰሉ ጉዳዮች ጭምር በግልጽ እና በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት አዋጁ ያስቀምጣል። የንግድ እቃው አገልግሎት የሚያበቃበት ጊዜ ሊቀመጥ ይገባል። በንግድ እቃው ላይ የሚለጠፉ መግለጫዎች በቀላሉ የማይለቁ ሊኾኑ ይገባል። ቢያንስ በአማርኛ እና እንግሊዘኛ መጻፍ እንዳለበት አዋጁ አስቀምጧል።
ሸማቹ ለሚገዛው እቃ ዋስትና እና ደረሰኝ የማግኘት መብት አለው፤ ነጋዴውም የመስጠት ግዴታ አለበት። ነጋዴዎች ለሰጡት ደረሰኝ ቀሪውን እስከ 10 ዓመት የመያዝ ግዴታ አለባቸው።
ማንኛውንም ጉድለት ያለበትን እቃ ወይም አገልግሎት እስከ 15 ቀን ድረስ የመመለስ፣ የመቀየር፣ የመተካት፣ የማስተካከል ወይም በድጋሜ አገልግሎት የማግኘት ሙሉ መብት አለው። “የተሸጠ እቃ አይመለስም” የሚለው አባባል ፈጽሞ የተከለከለ እንደኾነ ተቀምጧል። ሸማቹ ጉድለት ባለበት እቃ ለደረሰበት ጉዳት በሕግ ካሳ የማግኘት መብት አለው።
በነጋዴ እና በግለሰብ መካከል ቀድሞ የሚደረጉ ማንኛውም የውል ስምምነቶች በሕጉ ተቀባይነት የላቸውም።
አንድ የንግድ እቃ ወይም አገልግሎት ሸማቹ ሲገዛ ሌላ እቃዎችን ጨምሮ እንዲገዛ አይገደድም። የሚገዛው እቃ የሚለካው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ መለኪያዎች እንጅ በሚመለከተው ተቋም ወይም ባለሙያ ባልተረጋገጠ ባሕላዊ የመለኪያ መሳሪያዎች ለክቶ መሸጥ ወንጀል ነው።
አዋጁ እነዚህን እና ሌሎች ጉዳዮችን ለሸማቾች መብት ቢሰጥም በንግድ ላይ የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ባለመደረጋቸው ምክንያት ከዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመሠራቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ የንግድ እንቅስቃሴን ለመፍጠር በተዋረድ የሚገኙ የሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈጻሚ አካላት ማኅበረሰቡን በአቀናጀ መንገድ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባም ጠይቀዋል።
በተለይም ደግሞ በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር በሚጨመሩ፣ ምርት በሚደብቁ፣ ሚዛን በሚያጓድሉ አካላት ላይ ቅንጅታዊ አስተማሪ እርምጃ መውስድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!