“የተከዜ አዳኝ ትውልድ መጽሐፍ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለማንነቱ ያደረገውን ተጋድሎ የሚያሳይ ነው” የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ

69

ጎንደር: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የተጻፈው “የተከዜ አዳኝ ትውልድ” መጽሐፍ በጎንደር ከተማ ተመርቋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ “የተከዜ አዳኝ ትውልድ መጽሐፍ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለማንነቱ ያደረገውን ተጋድሎ የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

አቶ አማረ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ለነፃነቱ እና ለማንነቱ ያደረገውን ተጋድሎ እንዲሁም ለወደፊት ለኅብረተሰቡ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ከነመፍትሔው ላበረከቱት ለጸሐፊው ለአቶ አሸተ ደምለው ምሥጋና አቅርበዋል።

ለሌሎች የታሪክ ጸሐፍት ማጣቀሻ መኾን የሚችል መጽሐፍ ነው የተፃፈው ያሉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ መጽሐፉ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነትን የሚገልጽ ነው ብለዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ሕዝብ ላይ ጥናት እና ምርምር የሠሩ እንዲሁም በተከዜ አዳኝ ትውልድ መጽሐፍ ላይ በሃያሲነት የተሳተፉት ባምላክ ይደግ(ዶ.ር) በበኩላቸው መጽሐፉ ለሀገር አንድነት፣ ለሕዝብ ነፃነት እና ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው ብለዋል።

መጽሐፉ ከግነት ነጻ የኾኑ፣ በእውነት ላይ የተመሠረቱ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ማካተቱንም ዶክተር ባምላክ አስታውቀዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ታሪክ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጸሐፍት ተጽፏል ያሉት ጸሐፊው አሸተ ደምለው የተፃፈን ታሪክ ለመድገም ሳይኾን ኅብረተሰቡ የሚፈልገው ሰላም፣ ልማት እና ፍትሕ በመኾኑ አሱን ለማሳየት ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት የተደረጉ ትግሎች የእውነት እና የፍትሕ መኾናቸውን ለማሳወቅ መጽሐፉ እንደተጻፈም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ እና ባሕር ዳር ከተሞች የመጽሐፉ የምረቃ መርሐ ግብር እንደነበር ያስታወሱት አቶ አሸተ መጽሐፉ በአንባቢያን ዘንድ ተመራጭ እንዲኾን ከግነት የጸዳ ተደርጎ ተጽፏልም ብለዋል።

በ214 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ በወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ትግል እና ነፃነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ የክብር እንግዶችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ- አዲስ አለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከየካቲት 25 እስከ 29/2016 ዓ.ም በዘመቻ ይሰጣል።
Next article“የንግዱ ዓለም ሥነ ምግባር”