
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከየካቲት 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በልዩ መልኩ እድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች በዘመቻ እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የእናቶች፣ አፍላ ወጣቶች እና ሕጻናት መሪ ሥራ አስፈፃሚ የክትባት ቡድን አማካሪ ተመሥገን ለማ በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ስጋት የሆነው የማህጸን በር ካንሰር በገዳይነቱ በ2ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ልቅ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ለቫይረሱ መፈጠር ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል። የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ከየካቲት 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በልዩ መልኩ እድሚያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች ብቻ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጥ የነበረውን ክትባት አንድ ጊዜ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን አማካሪው ተናግረዋል። ትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የቅድመ መከላካል ሥራ እንደሚሠራ መጠቆማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ በዓመት በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት 5 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸው የሚያልፍ ሲሆን እድሚያቸው ከ14 ዓመት በላይ ከሆኑት ሴቶች ከአምስቱ አራት የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!