
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻያ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሸ ደሴ (ዶ.ር) በከተማው እየተገነቡ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ነጻነት መንግሥቴ፤ በከተማው ከሚገኙ 57 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው ብለዋል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተጀመረው ንቅናቄም 12 ነባር ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ለማድረግ ከ60 በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ቀደም ሲል በጭቃና እንጨት የተሰሩ ሦስት ትምህርት ቤቶችን ገፅታ ለመቀየር የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቶቹ የግንባታ ሥራ እየተካሄደ የሚገኘው በከተማ አስተዳደሩ፣ በአማራ ልማት ማኅበር፣ በዳሽን ቢራ አክሲዮን ማኅበር፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና ውጭ በሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የገንዘብ ድጋፍ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአዘዞ ክፍለ ከተማ በ65 ሚሊዮን ብር ወጪ 12 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሁለት የመማሪያ ህንጻዎች አስገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ልጅዓለም ጋሻው ናቸው፡፡
የህንጻዎቹ ግንባታ ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ አንድ ቤተ መጻህፍት፣ ሁለት ቤተ ሙከራና አንድ የአይሲቲ ማዕከል ማካተቱንም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የከተማው ትምህርት ቤቶች የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታና የትምህርት ጥራት ጉድለቶችን በተመለከተ ጥናትና ምርምር በመስራት ምክረ ሃሳቦችን ለከተማ አስተዳደሩ በማቅረብ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሸ ደሴ (ዶ.ር) በበኩላቸው፤ በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመሻገር የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ያሉ የትምህርት ዘርፍ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጎንደር ከተማ በትምህርት ዘመኑ በከተማው በሚገኙ 57 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ከከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!