የኢትዮጵያ ሕጻናት በሕገ ወጥ ደላላዎች ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚወጡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

41

አዲስ አበባ: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሕጻናት በሕገ ወጥ ደላላዎች በጂቡቲ፣ በሶማሊያ እና በኬንያ በኩል በሕገወጥ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚወጡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። ባለፉት ሁለት ዓመታትም ከ25 ሺህ በላይ ሕጻናት በሕገ ወጥ መንገድ ፈልሰው እንዲሄዱ መደረጋቸው ተነግሯል፡፡

ፍልሰቱም በሕጻናት ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የወሲብ ጥቃት እና የጉልበት ብዝበዛ ጉዳት እያደረሰባቸው ይገኛል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግም ፍልሰቱን ለመከላከል እና በፍልሰቱ ምክንያት ለተጎዱ ሕጻናት ድጋፍ ለማድረግ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአይኦኤም፣ ከሴቭ ዘ ችልድረን እና ከዩኒሴፍ ጋር በመተባባር ከሶማሊያ፣ ከኬንያ እና ከጂቡቲ ሀገር ተወካዮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በሕገወጥ መንገድ በሚደረጉ ፍልሰቶች ምክንያት በሕጻናት ላይ ጉዳት ከሚደርስባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መኾኗን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናግረዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ ፍልሰቱን ለመከላከል እና ከፍልሰቱ በኋላ ተጎጂ ለኾኑ ሕጻናት መደረግ ስላለባቸው እርዳታዎች ውይይት ለማድረግ ምክክሩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ሕጻናትን በማታለል በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ የሚያደርጉ ሕገወጥ ደላላዎችን በሕግ ጥላ ስር ለማዋል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሕግ ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት ሴቶች እና ሕጻናት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት እንዳይፈልሱ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሠራ መኾኑም ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleችግር ውስጥ ኾኖም የግንባታ ሥራዎችን በውጤታማነት ማከናወን መቻሉን የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ገለጸ።
Next articleበጎንደር ከተማ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻያ ግንባታ እየተካሄደ ነው።