ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ የዐረብ ሀገራት ድጋፍ እንዲሰጧት ጠይቃለች፡፡ ሁኔታው ኢትዮጵያ ለዚህ ክስ የሚመጥን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ ካልቻለች ግብጽ በዙሪያዋ ብዙ ሀገራትን ለማሰባሰብ እንደማይቸግራት አመላካች ሆኗል፤ ከሰሞኑም ግብጽ ብቻዋን አለመሆኗን ስትገልጽ እንደነበርም አይዘነጋም፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺኩሪ ለዐረብ ሊግ አባላት ኢትዮጵያ በ2015 (እ.አ.አ) የተፈረመውን መሠረታዊ የስምምነት መርህ እንድታከብር የሀገራቱ እገዛ እንደሚያስፈልጋት ጠይቀዋል፡፡ ነገርየው ሲገለጽ ‹‹ኢትዮጵያ መርሁን ጥሳለች ሳይሆን ባትጥስም በመርሁ እንዳትጠቀም በጋራ እናደናቅፍ›› ይመስላል፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ እያደገ የመጣውን ተሰሚነቷን ለመቀነስ የፈጠረችው ሴራ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ ግብጽ በሊጉ አድራጊ ፈጣሪ መሆኗና የኢትዮጵያና የዐረብ ሀገራት ግንኙነት ገና ታዳጊ መሆኑ በአጸፋው ኢትዮጵያን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ እንድትሠራ የሚጠይቅ የቤት ሥራ ነው ግብጽ መስጠት የፈለገችው፡፡
ኢትዮጵያ የዐረብ ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ትኩረቷን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ስታዞር ግብጽ በምትኩ ምዕራባውያኑን ከጎኗ ለማሰለፍ እንደምትሯሯጥም ይጠበቃል፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት ረቡዕ ካይሮ ውስጥ በተካሄደው የዐረብ ሊግ 153ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ ባደረጉት ንግግር ‹‹ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የውኃ ሙሊት እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከግብጽና ሱዳን ጋር ስምምነት ላይ ሳይደረስ ማድረግ እንደሌለባት በ2015 (እ.አ.አ) የተደረሰውን ስምምነት እንደጣሰች አድርገው አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ በስምምነቱ የአካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናቶች መካሄድ እንዳለባቸው እምነት እንዳላቸው ጠቁመው ‹‹ግድቡ በተፋሰሱ ሀገሮች ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ሳይንሳዊ መረጃ ሁሉ ለመደበቅ ኢትዮጵያ መሰናክሎችን እየፈጠረች ነው›› ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዐረብ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ታዲያ ግብጽ ይህን ግንኙነት ለማሻከር እና አንዳንድ ሀገራት ኢንቨስት ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመግታት እየሠራች መሆኑን ተከትሎ የተሻለ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በቀጣናው በመፍጠር የተሻለ ግንኙነት መፍጠርን ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡- አል አህራም ኦንላይን
በምሥጋናው ብርሃኔ