ችግር ውስጥ ኾኖም የግንባታ ሥራዎችን በውጤታማነት ማከናወን መቻሉን የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ገለጸ።

32

ደሴ፡ የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የ2016 በጀት ዓመት የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸምን በደሴ ከተማ እየገመገመ ነው ።

የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ታደሰ ግርማ ድርጅቱ በክልሉ እና ከክልሉ ውጪ የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳሉት ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት በአማራ ክልል ብቻ 37 የሕንፃ እና 5 የመንገድ ፕሮጀክቶችን እየገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት በድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢፈጥርም በችግር ውስጥ ኾኖም ውጤታማ የግንባታ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
በየጊዜው የሚያሻቅበው የገበያ ዋጋ ድርጅቱ ቀድሞ ከገባባቸው ውሎች ጋር አለመጣጣም ባለፉት ሰባት ወራት የተስተዋለ ችግሮች ስለመኾኑ በመድረኩ ተጠቅሷል።

ዋና ሥራ አሥፈፃሚው እንደገለጹት ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ሠራተኞች በችግር ውስጥ ኾነው ውጤታማ ሥራ የመሥራት አቅም እንዲያጎለብቱ ይደረጋል ነው ያሉት። ድርጅቱ ወቅታዊ የገበያ ዋጋን ተመርኩዞ ከፕሮጀክት ባለቤቶች ጋር ውል የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።

በደሴ ከተማ የሦስት የግንባታ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አሻግር መለሰ እና የወልድያ ዙሪያ ፕሮጀከቶች አስተባባሪ አለባቸው አባተ በክልሉ የሰላም መደፍረስ ቢያጋጥምም በተቻለ አቅም ግንባታዎች እንዲቀጥሉ ተደርጓል ብለዋል።

የግንባታ ሥራዎች የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች በመኾናቸው ማኅበረሰቡ ለድርጅቱ ሥራዎች ውጤታማነት ተባባሪ ስለመኾኑም ተናግረዋል። በግምገማ መድረኩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚመሩ ማናጀሮች ፣ የፋይናንስ አስተባባሪዎች እና መሀንዲሶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየገቢዎች ሚኒስቴር፣ አማራ ባንክ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር በጋራ አገልግሎት ለመስጠት ስምምነት አደረጉ።
Next articleየኢትዮጵያ ሕጻናት በሕገ ወጥ ደላላዎች ወደተለያዩ ሀገራት እንደሚወጡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።