
አዲስ አበባ: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሦስትዮሽ ስምምነቱም የታክስ ክፍያን በኤሌክትሮኒክስ ዜዴ ለመሠብሰብ ዓላማ ያደረገ ነው።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ንግግር ያደረጉት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት መስቀሌ የዲጅታል ገቢ አሥተዳደር ሥርዓት ለአገልግሎት ተቀባዩ ግልፅ፣ ቀላል እና ተደራሽ አገልግሎት ለመሥጠት ያስችላል ብለዋል።
ስምምነቱ በባንክ ታክስ ከፋዩ በፈለገው ጊዜ ውስጥ ባለበት ቦታ ኾኖ ታክሱን ቀልጣፋ በኾነ መንገድ መክፈል እንዲችል እና የተፈጸመው ክፍያ ደኅንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ያስችለዋል ሲሉ ነው የገልጹት።
ከአሁን በፊት ከ17 ባንኮች ጋር የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸውን የገለጹት ወይዘሮ መሠረት እስከ ጥር 30/2016 ዓ.ም ድረስ ካሉት ግብር ከፋዮች 45 ሺህ 212 ወይም 93 በመቶ የሚኾኑት በኤሌክትሮኒክስ ታክስ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል። 53 በመቶ የሚኾኑት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ እየፈጸሙ መኾኑን ተናግረዋል። ሥርዓቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ከሀገር ውስጥ ታክስ 182 ቢሊዮን ብር በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የአማራ ባንክ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጫንያለዉ ደምሴ የአማራ ባንክ የሀገራችንን የክፍያ ሥርዓት ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ፣ ለተገልጋዩ ኅብረተሰብም አካታች፣ አስተማማኝ እና ቀላል እንዲኹም ከጥሬ ገንዘብ ነፃ የኾነ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር በሚደረገው የዲጅታል ባንኪንግ አገልገሎት አሰጣጥ ዙርያ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ የተደረገው ስምምነትም የግብር አከፋፈል ሥርዓቱን የሚያዘምን እና የደንበኞችን ድካም የሚቀንስ በመኾኑ የትብብር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ነው የገለጹት።
ዲጅታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም ባንኩ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሐሚድ የክፍያ እና ትራንዛክሽን ጉዳይ በጣም ክትትል የሚፈልግ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በመኾኑም በጋራ መሥራታችን በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የታክስ ሥወራ ለመከላከል ያስችላል ብለዋል። ሌሎች ባንኮችም ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ እና የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን እቅዳችንን ለማሳካት በጋራ የምንሠራበትን አካሄድ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ሲሉም ዋና ዳይሬክተሯ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!