የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም መስበክ እንደሚገባቸው የኮረም ከተማ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

27

ሰቆጣ: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ እንዲቀጥል ሰላምን መስበክ እንደሚገባቸው የኮረም ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት አባቶች ተናግረዋል። ኮረም ከተማ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ካሉ ጥንታዊ ከተሞች አንዷ ስትኾን በውስጧም የተለያዩ የእምነት ተከታዮች በመተባበር እና በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ ናት።

የኮረም ከተማ የሃይማኖት ፎረም ሠብሣቢ በኩረ ትጉሃን ቆሞስ ጸጋይ አበበ “ራሱ ሰላም የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስን በመስበክ ሀገር ሰላም እንድትኾን ማስተማር እና መጸለይ የሃይማኖት አባቶች የዘወትር ሥራችን ሊኾን ይገባል” ብለዋል።

ቤተ ክርስትያን ድምጿን ከፍ አድርጋ “ስለ ሰላም ጸልዩ” ስትል ወጣቱ ትውልድ ሊያደምጣት ይገባል ነው ያሉት በኩረ ትጉሃን፡፡ “ችግሮች መከሰታቸው የዓለም ጠባይ ነው ነገር ግን ችግሮችን በሰላም የመፍታት ጠባይ የተሰጠው ሰው ነገሮችን ማገናዘብ አለበት” ሲሉም አስገንዝበዋል።

የሃይማኖት ፎረሙ አባል ሙሐመድ ሰይድ “እስላም ማለት በራሱ ሰላም ማለት ነው እና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንደስሙ ለሰላም ሊሠራ ይገባል” ብለዋል።
ሀገሪቱ ብሎም ክልሉ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል ኹሉም ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማትም የእምነቱ ተከታዮች ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ ከልባችው እንዲሠሩ ማስተማር እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመማር ማስተማሩ ሥራ በአግባቡ እየተከናወነ መኾኑን ወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
Next articleበአማራ እና ትግራይ ክልል ለሚገኙ አርሶ አደሮች የአትክልት እና ፍራፍሬ ዘር ድጋፍ ተደረገ።