
ባሕር ዳር፡ የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ ደሴ ከተማ የሚገነባውን ባለ14 ወለል ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሕንጻ የግንባታ ሂደትን ባደረገው ጉብኝት ገምግሟል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአምስት መቶ 44 ሚሊየን ብር በላይ በኾነ ወጭ ደሴ ከተማ ላይ ባለ14 ወለል የሚዲያ ሕንጻ እየገነባ ነው።በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት እና አደረጃጀት አማካሪና የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ ሲሳይ አሚኮ እና አማራ ሕንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ተናበውና ጥብቅ ክትትል በማድረግ ለዚህ ደረጃ ማብቃታቸውን አመሥግነዋል ።
አቶ ይርጋ የግንባታ ፕሮጀክቶች ጥብቅ ክትትል የሚፈልጉ በመኾናቸው በቀጣይም ጥብቅ የግንባታ ክትትሉ ከሁለቱም ወገን ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።የአሚኮ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት በበኩላቸው ይህ ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ሕንጻ ለአማራ ክልል ብቻ ሳይኾን ለአጎራባች ክልሎችም ትልቅ የሚዲያ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የሕንጻው ግንባታ ሲጠናቀቅ አሁን ላይ የተጨናነቀውን የአማራ ኤፍኤም ደሴ 87.9 የሥራ ቦታ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻግረዋል ብለዋል።የሕንጻው ግንባታ በተያዘው ውል መሠረት ሰኔ /2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።ሕንጻው ያረፈው 860 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው። በዚህ ወቅት ግንባታው 26 በመቶ ደርሷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!