
ባሕር ዳር: የካቲት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል 82 በመቶ የሚኾነው ሥነ ምሕዳር ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ መኾኑን የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። በክልሉ ከ7 ሺህ በላይ የቀሰም አበባ እጽዋት ዝርያዎች፣ የሀገር በቀል ዛፎች ክምችት እና የተለያዩ ጥብቅ ደኖች መገኛ መኾኑ ይበልጥ ምቹ አድርጎታል።
በክልሉ ምዕራብ ጎጃም፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ብዛት ያለው አናቢ የሚገኝባቸው አካባቢዎች በመኾናቸው ከፍተኛ የማር ምርት ይመረትባቸዋል፡፡ የተከዜ ተፋሰስ፣ ሰሜን ወሎ፣ የጎንድር ቆላማ እና የአባይ ሸለቆ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚመረተው ማር ደግሞ ዓለም አቀፍ የጥራት መመዘኛ መስፈርቱን ያሟላ የማር ምርት የሚመረትባቸው አካባቢዎች ናቸው። ጥራት ያለው ማር ከሚመረትባቸው የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ውስጥ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አምደወርቅ ከተማ እና አካባቢው በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማሩ አምራቾች ውስጥ አቶ አለባቸው በላይ አንዱ ናቸው። አቶ አለባቸው በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማሩ 10 ዓመታትን አሥቆጥረዋል። ታዲያ ያለፉበት መንገድ ከባሕላዊ አሠራር ያልተላቀቀ በመኾኑ የሚያገኙት የማር ምርት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ያለፈ እንዳልነበር ነግረውናል፡፡
ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታ ውስጥ ካላቸው 36 ቀፎዎች ወስጥ 15 ቱን ወደ ዘመናዊ ቀፎ መቀየራቸውን ገልጸውልናል፡፡ በዚህም ከዚህ በፊት ከአንድ ባሕላዊ ቀፎ ያገኙ የነበረውን ከ10 ኪሎ ግራም የማይበልጥ ማር በአማካይ እስከ 25 ኪሎ ግራም ማግኘት መቻላቸውን አንስተዋል። አሁን ላይ በአካባቢ ገበያ ለኪሎ 700 ብር እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት ከ15 ዘመናዊ ቀፎ በአንድ የማር ምርት ወቅት ከ262 ሺህ ብር በላይ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት ከቻሉ ደግሞ ከእርሻ በተጓዳኝ ከ520 ሺህ ብር በላይ ገቢ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡
አቶ አለባቸው እንዳሉት ከማር ምርት በተገኘው ገቢ የእርሻ እና የወተት ከብቶችን መግዛት ችለዋል፤ የከተማ ቤት ገንብተዋል፤ አምስት ልጆቻቸውንም አስተምረዋል፡፡
በቀጣይ ባሕላዊ ቀፎዎችን ሁሉ ወደ ዘመናዊ ለመተካት እና ቁጥሩንም ለማሳደግ እቅድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለንብ ማነብ ሥራው የሚያስፈልጉ ተጨማሪ ዘመናዊ ቀፎዎችን፣ ሌሎች ግብዓቶችን እና ሥልጠናዎች በተደራጀ መንግድ መሥጠት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብ እና ሃር ልማት ባለሙያ ሙሐመድ ጌታሁን እንዳሉት በ2016 ዓ.ም በክልሉ ከሚገኘው ከ480 ሺህ በላይ አናቢ ከ30 ሺህ 100 በላይ ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ ነበር፡፡ በስድስት ወሩ ከ13 ሺህ 985 ቶን ማር ማምረት ተችሏል፡፡ ይህም ከዓመቱ 46 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ከፍተኛ ማር በሚመረትባቸው አካባቢዎች ድርቅ መከሰት፣ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ድጋፍ ለማድርግ እና ግብዓት ለማቅረብ ባለመቻሉ ምርቱን በታቀደው መጠን ለማምረት እንቅፋቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።
በ2015 ዓ.ም በነበረው የተሻለ የዝናብ ሥርጭት እና አንጻራዊ ሰላም ባለፉት አሥር ዓመታት ከተመዘገበው የማር ምርት በተሻለ ማምረት መቻሉን ባለሙያው አንስተዋል፡፡ የተቀመጡ የአስተዳደር ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ በአማካኝ እስከ 30 ኪሎ ግራም ማር ምርት ማግኘት መቻሉንም ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ለአረም እና ለአንበጣ በየጊዜው የሚረጨው ኬሚካል አጠቃላይ ለንብ ማነብ ሥራው ፈተና እየኾነ መምጣቱን ነው ባለሙያው ያነሱት። የዘመናዊ ቀፎ፣ የማር ማጣሪያ እና የመሳሰሉ የንብ እርባታ ግብዓቶች እና ቴክኖሎጅዎች ዋጋ መናር ማኅበረሰቡ ካለበት የኢኮኖሚ ችግር ጋር ተዳምሮ ወደ ዘመናዊ ንብ እርባታ ለመሸጋገር ሌላው ፈተና ኾኗል፡፡ ከዚህም ባለፈ የእውቀት፣ ሥልጠና እና የበጀት ችግር ማነቆ መኾኑን ገልጸዋል።
የሀገሪቱን የማር ምርት ለማሳደግ አሁን በክልሉ ያለውን 95 በመቶ የሚኾነውን ባሕላዊ አናቢ ወደ ዘመናዊ አናቢ ማሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ድጎማ ማድረግ እንዳለበት ነው የመከሩት።
ከዚህም ባለፈ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት፣ ለአናቢዎች ሥልጠናዎችን ማስፋት እና ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!