“የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ዝግጁ ነን” የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት

81

ደሴ: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ እና በደቡብ ወሎ ዞን ለተመደቡ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በደሴ ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ለአባላቱ የደሴ እና የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የቀድሞው የልዩ ኃይል አባላትም በቆይታቸው ጠቃሚ ሥልጠና ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል። የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የክልሉ መንግሥት ለአማራ ሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በመለየት እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል። የጸጥታ አባላትም ለሰላሙ እንዲሠሩ ሲሉ አሳስበዋል። የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ሀገር የኅልውና አደጋ ውስጥ በገባችበት ወቅት የቁርጥ ቀን ደራሽ መሆኑን አስመስክሯል ያሉት አቶ ሳሙኤል አሁንም የሕዝብን እና የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ፤ መንግሥትም የጸጥታ ኃይሉን ለመደገፍ እንደሚሠራ ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈላችሁትን መስዋዕትነት አንረሳውም ብለዋል። የአማራ ሕዝብ አሁንም ለችግር እየተዳረገ እና እየተዘረፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአማራ ሕዝብ ባሕል እና እሴት የወጡ አሳፋሪ ተግባር እየተሠራ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው የጸጥታ አባላቱም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በድጋሜ የሕዝብን ሰላም እንድታረጋግጡ ሲሉ አሳስበዋል።

የ801ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በበኩላቸው የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ሀገርን የታደገ ኃይል መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያዊነቱን እና ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ አባላት ነው ብለዋል። በቀጣይም አባላቱ ከሠራዊቱ ጋር በመቀናጀት ሕዝባዊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አሰፋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በ4 ቢሊዮን ብር 3 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ ገለጸ።
Next articleግዙፉ ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ በቅርቡ ተመርቆ ምርት ማምረት እንደሚጀምር የክልሉ መንግሥት ገለጸ።