
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአዳሪ ትምህርት ቤት የግንባታ የመሰረት ደንጋይ ተቀምጧል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኅላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሀይ በጋራ የመሰረት ደንጋዩ አስቀምጠዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ቢሮ ኀላፊዋ በአማራ ክልል በ4 ቢሊዮን ብር 3 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።
ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የተሻሉ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ተጠቅመው በመማር ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያግዛሉ ብለዋል ዶክተር ሙሉነሽ።
ለትምህርት ቤቶች በአመለካከት፣ በአስተሳሰብ እና በእውቀት የተሻሉ መምህራን እንደሚመደቡም ጠቁመዋል ።
ለትምህርት ጥራት የጋራ ርብርብ በማድረግ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እና ትውልድን በልዩ ትኩረት መገንባት እንደሚገባም አሳሰበዋል። “ትምህርት ላይ በልዩ ትኩረት መሥራት ከቻልን በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ መኾን እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል ።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፣ ኮሌጆች እና ዲያስፖራዎች ለትምህርት ዘርፍ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል ።ዛሬ የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠለት አዳሪ ትምህርት ቤት የሚገነባው በዳሽን ቢራ እና በጎንደር ዩንቨርሲቲ መሆኑም ተገልጿል። ዶክተር ሙሉነሽ ግንባታው በፍጥነት ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንዲገባ አሳሰበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ትምህርት ቤቱ ለአርሶ አደሮች 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ካሳ በተከፈለበት 4 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል ።
ግንባታው እስኪጠናቀቅ የአካባቢው ኅብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደረግ ከንቲባው አሳሰበዋል።ዛሬ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ትምህርት ቤት በትምህርታቸው ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎች ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተሰባስበው የሚማሩበት ነው ብለዋል።
ጎንደር አዳሪ ትምህርት ቤት በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መኖሩን ያስታወሱት ከንቲባው በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመገንባት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ትውልድን ለመገንባት ትምህርት ቤቶች የራሳቸው ድርሻ አላቸው፤ የትምህርት ቤቶችን ገፅታ ለመገንባት ደግሞ ባለሃብቶች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!