የበለስ-መካነ ብርሃን የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚኮን ተገለጸ።

29

ባሕር ዳር፡ የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን የበለስ-መካነ ብርሃን የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ አስታውቋል።

ፕሮጀክቱ 39 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ የጃናሞራ፣ የበየዳ፣ የደባርቅ ወረዳዎችን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን ማገናኘት የሚችል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

የፕሮጀክቱ ስር 10 ድልድዮች የሚገነቡ ሲኾን ግዙፍ የኾነው ባለ160 ሜትር ርዝመት የበለገዝ ድልድይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። በበለገዝ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ መጠናቀቅም በክረምት ወራት በወንዝ ሙላት ሲቸገሩ የነበሩ አጎራባች ወረዳዎችን ችግር የሚፈታ እንደሆነ ተገልጿል።

የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን ደመቀ፤ በኢንተርፕራይዙ የተደረጉ የለውጥ ማሻሻያ እርምጃዎች ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ እያስቻለ ነው ብለዋል።

የበለስ-መካነ ብርሃን የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ፕሮጀክትን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ አስቸጋሪ የሆኑ የተራራ ቆረጣ ሥራዎችን በማጠናቀቅ መንገዱን በሚቀጥለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
የበለስ-መካነ ብርሃን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ተስፋ ዘለቀ፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ አሁን ላይ 65 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የመንገዱን ግንባታ በተመለከተ የመስክ ምልከታ ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ባያብል ሙላቴ፤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉትን የበለስ-መካነ ብርሃን የመንገድ ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የመንገዱ ግንባታ እውን መሆን የኅብረተሰቡን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ወሳኝ መሰረተ ልማት መሆኑን አንስተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም፤ የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የበለገዝ ወንዝ ድልድይ መጠናቀቅ በክረምት ወራት የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍትሔ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ግንባታ ሥራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀላሉ ለገበያ ማቅረብ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርና የምጣኔ ሃብት እድገትን ለማሳለጥ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት አምስት ዓመታት የተካሄዱ የአዲስ ወግ ውይይቶችን የሰነደ “የአዲስ ወግ መድረኮች” መጽሐፍ ዛሬ ተመረቀ፡፡
Next article“ሥልጠና አጠናቃችሁ የአድማ ብተና አባላትን ስትቀላቀሉ የሕዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ አደራ ተጥሎባችኋል” የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን