በዝቋላ ደብረ ከዋክብ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት አባቶች የተፈጸመውን ግድያ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አወገዘ።

92

አዲስ አበባ፡ የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዝቋላ ደብረ ከዋክብ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት አባቶች የተፈጸመውን የግፍ ግድያ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አውግዟል።

መንግሥት ለቤተክርስቲያኗ እና ለዜጎች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የግፍ ግድያውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

መንግሥት በቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ እንዲያጣራ እና የወንጀል ተግባሩን የፈጸሙትን ለሕግ እንዲያቀርብ እና የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የሃይማኖት ተቋማትን እና መዋቅራቸውን ሁሉ በሕግ ከተቋቋመበት መንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ ለኾነ ተግባር ለፖለቲካዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ ተልዕኮው መጠቀሚያ እንዳያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መንፈሳዊ ነጻነታቸው እንዲከበር ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ያስገነዘቡት።

በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች እና አስተማሪዎች ከመሠረታዊ የሃይማኖት አስተምህሮ ዶግማ እና ቀኖና የሚቃረን ፖለቲካዊ አቋም ከማራመድ እንዲቆጠቡ በአጽንኦት አሳስበዋል።

መንግሥት እየተፈጸሙ ያሉ እገታና የደኅንነት ሥጋቶችን በማስወገድ የዜጎችን የመንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብት የማስጠበቅ መንግሥታዊ እና ሕጋዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ድርቁን እያሸነፍን ነው” የአበርገሌ ወረዳ አርሶ አደሮች።
Next articleባለፉት አምስት ዓመታት የተካሄዱ የአዲስ ወግ ውይይቶችን የሰነደ “የአዲስ ወግ መድረኮች” መጽሐፍ ዛሬ ተመረቀ፡፡