“ድርቁን እያሸነፍን ነው” የአበርገሌ ወረዳ አርሶ አደሮች።

24

ባሕርዳር: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ሃላዩ መኮንን የአበርገሌ ወረዳ ነዋሪ ሲኾኑ በድርቁ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ያለፈው ክረምት ዝናቡ ወጣ ገባ በመኾኑ የዘሩት እህል ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን ገልጸዋል፡፡ ድርቁ ከባድ ስለነበር ለከብቶቻቸው የሚያቀርቡት መኖ በማጣጣታቸው መጎዳታቸውንም ነው የነገሩን፡፡

ነገር ግን የመስኖ አማራጭ ተጠቅመው ፈጥነው የሚደርሱ እንደ ሽንኩርት፣ በቆሎ እና ማሽላ የመሳሰሉ ሰብሎችን በመዝራት ድርቁን ማሸነፍ እና ለከብቶቻቸውም መኖ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የዝቋላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አብራው ዘገየ ድርቁ በከብቶችም በሰዎችም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ መሄዱን ነው ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ግን ከወረዳው የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር ውኃ ገብ መሬት ተጠቅመው ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችን በመዝራት ከችግሩ ለመውጣት ጥረት እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡ በሠሩትም ሥራ ማሽላ እና በቆሎ ዘርተው አሁን እንደደረሰላቸው እና ከችግራቸው እንዳወጣቸው ገልጸዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲሱ ወልዴ በ2015/16 የክረምቱ ዝናብ ወጣ ገባ ስለነበር በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሦስት ወረዳዎች ላይ ድርቅ መከሰቱን እና ጉዳት ማስከተሉን አስታውሰዋል፡፡ በተለይ በሰሃላ ሰየምት ሙሉ በሙሉ፣ በአበርገሌ እና በዝቋላ በከፊል ድርቁ ጉዳት እንዳደረሰ ነው የገለጹት፡፡

ጉዳቱን ለመቀነስ ያሉትን አማራጮች መጠቀማቸውን አስረድተዋል፡፡በተለይም ከችግሩ ለመውጣት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉትን የውኃ አማራጮች በመለየት ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎች ተዘርተዋል ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን ድርቅ ሲከሰት የውኃ አማራጮች የሚቀንሱ ቢኾንም ባለው መጠን ሳይባክን ለምግብ የሚኾኑ አዝዕርት እና የከብቶችን መኖ ለማልማት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 6 ሺህ 33 ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑንም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።
መምሪያ ኀላፊው አሁን ላይ አዝዕርቱ ደርሶ ችግሩን እያቃለለ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ በቆሎ፣ ቲማቲም፣ ማሽላ እና ሽንኩርት አሁን ላይ ደርሰው እየተሠበሰቡ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደቡብ ወሎ ዞን 23ሽ 859 ሄክታር መሬት በአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ መሸፈኑ ተገለጸ።
Next articleበዝቋላ ደብረ ከዋክብ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት አባቶች የተፈጸመውን ግድያ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አወገዘ።