“ባለፉት ስድስት ወራት 176 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከ1 ሺህ 280 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል” አቶ እንድሪስ አብዱ

38

ደሴ: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ ወራት አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በበጀት ዓመቱ ለ5 ሺህ 600 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ ሲሠራ መቆየቱን የቢሮው ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ገልጸዋል። “ባለፉት ስድስት ወራት 176 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ከ1 ሺህ 280 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል” ሲሉም የቢሮውን የእቅድ ክንውን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል የተከሰተው የፀጥታ ችግር በክልሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ይህም ቢሮው ባቀደው ልክ እንዳይሠራ አድርጎታል።
በዘርፉ የታቀደውን ያህል ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ቢገቡ በፕሮጀክቶቻቸው ለ226 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችሉ ነበር።

በስድስት ወራት ለ28 ሺህ ዜጎች በዘርፉ የሥራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ቢኾንም እስካሁን የተፈጠረው የሥራ ዕድል 8 ሺህ 945 ብቻ መኾኑን እና አፈጻጸሙም 32 በመቶ መኾኑን ቢሮ ኀላፊው እንድሪስ አብዱ ለአሚኮ ተናግረዋል። በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት የኢንቨስትመንት ፍስሰቱን በመቀነስ በሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ያሳያልም ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ 89 ኢንዱስትሪዎች 41 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ማምረታቸውን እና የውጭ ምንዛሬ ማዳናቸውን ቢሮ ኀላፊው ገልጸዋል። 19 ኢንዱስትሪዎች እና ስድስት የአበባ ልማት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወደ ውጭ ከላኩት ምርት ከ35 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘታቸውንም ጠቁመዋል።

በክልሉ አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራውን እና አጠቃላይ የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መኾኑም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል። ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ተብሏል።

የግምገማ መድረኩ የቢሮውን ኀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ነው።

ዘጋቢ:- አሊ ይመር

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleይካቲት 15/2016 ም.አ ቺርቤዋ ጋዚቲ
Next articleከላሊበላ – ሙጃ – ቆቦ አስፓልት መንገድ ሥራ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።