
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለአህጉሩ እና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች፤ እያበረከተችም ትገኛለች ሲሉ አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ተናገሩ።
አምባሳደር ቆንጂት ኢትዮጵያ አህጉራዊ የምጣኔ ሃብት ትስስር ለመፍጠር ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ አማካኝነት ለአህጉሩ እና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች፤ እያበረከተችም ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል አማካኝነት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን ዳርፉር፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን አዋሳኝ በኾነችው አቢዬ ግዛት የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በአግባቡ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል ነው ያሉት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በነጻነት ተምሳሌትነት ተነሳሽነትን በመፍጠር የተገደበ አይደለም ያሉት አምባሳደር ቆንጂት በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ የማድረግ ዓላማ የነበረውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት የመሪነት ሚና ተጫውታለች ብለዋል።
“አፍሪካ ወገቤን ባለች ጊዜ ሁሉ እንደ ኢትዮጵያ ደርሶ የደገፉ የሉም” ያሉት አምባሳደር ቆንጂት ኢትዮጵያ “የሞኖሮቪያ” እና “የካዛብላንካ” ቡድን በሚል ተከፍለው የነበሩትን የአፍሪካ ሀገሮች አዲስ አበባ ላይ በማገናኘት እና ልዩነቶችን በማለዘብ ወደ አንድ የጋራ አቋም እንዲመጡ አድርጋለች ብለዋል።
በዚሁ መሠረት ግንቦት 1955 ዓ.ም 32 መስራች ሀገሮች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በይፋ አቋቁመዋል። ለዚህ ድርጅት እውን መኾንም ኢትዮጵያ የመሪነት ሚና መጫወቷንም ገልጸዋል።
እንደ አምባሳደር ቆንጂት ገለጻ የአፍሪካ ሀገራትን ነጻነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተ እና ዓላማውን ያሳካው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረት እና ተልዕኮውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ተመስርቷል ያሉት አምባሳደር ቆንጂት የአፍሪካ ኅብረት በአዲስ የአፍሪካ ራዕይ እንዲፈጠር እና ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት እንዳደረገችው ሁሉ የጎላ ድርሻ ነበራት ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንና ቀደምት የሀገሪቱ መሪዎች ለአፍሪካ ነጻነት ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋጽኦ አስታውሰው አዲስ የተመሠረተው የአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲኾን አድርገዋል ያሉት አምባሳደር ቆንጂት ይህንን ትውልዱ ማስቀጠል አለበት ብለዋ ሲል ኢፕድ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!