
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትዕግስት ዋለ በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪ ናት። ከ2009 ዓ.ም በፊት ሥራ እየፈለገች ከወላጆቿ ጋር ትኖር ነበር። ሠርቶ በማደር ፈንታ የቤተሰብ ሌላ ጫና ኾኛለሁ ብላ ስለምታስብም ትጨነቅ ነበር። የመንግሥት ሥራ ለመቀጠርም የተለያዩ የሥራ አማራጮችን ስትሞክር ቆይታ በ2009 ዓ.ም ከሌሎች አራት ወጣቶች ጋር በኢንተርፕራይዝ ተደራጅታ ወደ ዶሮ እርባታ ሥራ ገብታለች። ”ሥራውን ስንጀምር እንቁላል የሚጥሉ ዶሮዎችን በማርባት ነበር” ያለችው ትዕግስት በሂደት ጫጩት ማስፈልፈል እና የሥጋ ዶሮ ማሳደግንም ጨምረው መሥራታቸውን ትናገራለች።
በአምስት መቶ እንቁላል ጣይ ዶሮ እና አንድ እንቁላል በሁለት ብር በመሸጥ የተጀመረው ሥራ ውጣ ውረድ የበዛበት፣ አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ትዕግስት ታስታውሳለች። ብድር ለማግኘት ዋስ ማጣት፣ የዶሮዎች መሞት፣ ያመረቱት እንቁላል መጠኑ ትልቅ እና በቀለሙም ከሀበሻ እንቁላል የተለየ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ሊላመደው አለመቻሉ የምታስታውሳቸው ችግሮች ናቸው።
እንደምንም ችግሮችን አልፈው በጀመሩት ሥራ ያመረቱትን እንቁላል ገበያ በመውሰድ እና በምግብ ቤቶች በማዞር ይሸጡ ነበር። ምርታቸውን ከሸማቾች ጋር ለማስተሳሰር ቢሞከርም የኅብረተሰቡ አለመፈለግ ሌላኛው ፈተና እንደነበር ታስታውሳለች። ገበያቸውን ለማለማመድም ዋጋ ቀንሰው ይሸጡ እንደነበር ነው ትዕግስት የምትናገረው።
በወቅቱ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ሥራዎች ማስፋፊያ እና ማደራጃ ተቋም ስለ እንቁላል አመራረት እና አያያዝ ሙያዊ ድጋፍ በማግኘት ከስድስት ወራት በኋላ ተጨማሪ ዶሮዎችን ቢገዙም ከነባሮቹ ጋር በዕድሜያቸው መለያየት ምክንያት እየተበላሉ መሞታቸው ሌላ መፍትሔ የሚሻ ችግር ነበር።
ለአካባቢው ፋና ወጊ የኾኑት እነትዕግስት ችግሮችን በመቋቋም በሂደት ውጤታማ እየኾኑ ነው። ከአዲስ አበባ የአንድ ቀን ጫጩቶችን አስመጥተው በ25 ብር ሂሳብ በመረከብም ማሳደግ ጀመረዋል። በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት የሙያ እና የሕክምና ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ሥራውን ከጀመሩ ከስድስት ወር በኋላ ከስህተቶች እና ከችግሮች ተምረው ተረጋግተው ሥራውን ቀጠሉበት።
ትዕግስት ”እየተወያየን እንሠራለን፤ የባለሙያ ድጋፍ ይደረግልናል፤ በዚህም ሥራችን ውጤታማ መኾን ጀመረ” ነው ያለችው። ከጊዜ በኋላም ድርጅታቸውን በማስፋፋት ጫጩት፣ እንቁላል እና እንቁላል ጣይ ዶሮ አቅራቢ እንደኾኑ ነው የምትናገረው።
በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የቀጠለው የእነትዕግስት ኢንተርፕራይዝ አንድ ጓደኛቸው ሲለያቸው በስተቀር እሷን ጨምሮ አራት ጓደኞቿ በደመወዝ ተቀጥረው እንዲሠሩ አደረጃጀት አበጁ። ከዕለት ኑሯቸውም አልፈው ገንዘብ ማጠራቀም ጀመሩ። አሁን ላይ የ200 ሺህ ብር ብድራቸውን ከፍለው ጨርሰዋል። በጥሬ ገንዘብ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ እንዳጠራቀሙ ነው ትዕግስት የገለጸችው። በቀጣይም ምርታቸውን እሴት ጨምረው ለገበያ ለማቅረብ እንዳቀዱ ትዕግስት ገልጻለች። ለዚህም ቦታ በሊዝ ገዝተው ድርጅታቸውን ማስፋፋት ይፈልጋሉ።
ትዕግስት በሥራ ፈጠራ ሕይወቷ ሂደት ብዙ ውጣ ውረድ አልፋለች። የመንግሥት አካላት በሚናገሩት ልክ በተግባር አለመገኘት፣ የአበዳሪ እጦት፣ ዋስ አለመገኘት፣ ምርትን ለመሸጥ የገበያ እጦት ፈተናዎች እንደነበሩ ትዘረዝራለች። የአንዳንድ የመሥሪያ ቤት ሠራተኞች መስተንግዶም አሰቃቂ መኾኑን ጭምር አስታውሳ ”ዓላማ ኖሮን በጽናት መታገል ግን ከችግር እንደሚያወጣ ልንገነዘብ ይገባል” ብላለች።
ሥራ ፈጣሪዎች በተለይ ወጣቶች በብድር ያገኙት ገንዘብ የሚመለስ ስለማይመስላቸው የሚያባክኑ አሉ። ከሥራው የሚገኘውን ገንዘብ አጠቃቀም ላይም ጥንቃቄ የጎደላቸው እንዳሉ ነው የትዕግስት ትዝብት።
የተሰጡትን ብድር ተከፋፍለው የጠፉም መኖራቸውን ጠቅሳ የሷ ኢንተርፕራይዝ ግን ችግሮችን ተቋቁሞ መዝለቁን ነው የገለጸችው። ”እንወያያለን፣ ብድራችንን በወቅቱ እንመልሳለን፣ በማዘግየት ተቀጥተንም አናውቅም” ብላለች። ብድር ለመመለስ ስንሄድም የሥራ ትጋታችንን ስላዩ በክብር ነበር የሚያስተናግዱን ብላለች።
”የሰው ልጅ ዓላማ ሊኖረው ይገባል፤ ሥራን ሳልንቅ ከሰራሁ ነገ የተሻልሁ ሰው እንደምኾን እርግጠኛ ነበርኩ” ያለችው ትዕግስት ”ሥራን ሳልንቅ እና ሳልሰለች ለተሻለ ሕይወት እየሠራሁ ነው” ስትልም ሳይታክቱ የመሥራትን ዋጋ ተናግራለች።
አሁን ላይ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም ችግር በኮቪድ 19 ጊዜ ካጋጠማቸው ችግር የከፋ መኾኑን ነው ትዕግስት የምትናገረው። በ45 ቀን ሊሸጡ የሚገባቸው ዶሮዎች በመንገድ መዘጋት ምክንያት ሰባት ወር መቆየቸውን ገልጻለች። ከመስከረም ወዲህ እስከ 4 ጊዜ ጫጩት አሳድገው መሸጥ እየቻሉ አንድ ጊዜ ብቻ መሸጣቸውን ተናግራለች።
ጫጩት ለማስመጣትም ኾነ ምርትን ለመላክ የመንገድ መዘጋት ስለሚኖር እስከ 120 ሺህ ብር ድረስ እናገኝ የነበረውን ገቢ አጥተናል ብላለች። ግጭቱ ጠንከር ሲልም አካባቢውን ለቀው በመውጣታቸው በጠባቂ እጦት ዶሮዎቻቸው በአውሬ እንደተበሉባቸው ገልጻለች።
ይሁንና በሰላም ችግሩም ውስጥ ኾነው ሥራውን መቀጠላቸውን ነው ትዕግስት የተናገረችው። ምንም እንኳ እንደ ሰላሙ ጊዜ ባይኾንም ዛሬም እየሠራን ነው ብላለች፡፡ ለደንበኞቻችን እየደወልን በማሳወቅ የጫጩትም ኾነ የሥጋ ዶሮ ምርታችንን እንሸጣለን ብላለች። ወቅታዊ አዝማሚያዎችን እያየን ሥራዎችን እየቀያየርን እንሠራለን እንጂ በጭራሽ አላቆምነውም ስትልም በጽናት እየሠሩ መኾኑን ትናገራለች።
ትዕግስት በዚህ ሥራ ከተሰማራች በኋላ በጽናት በመሥራቷ አሁን ላይ ራሷን ችላለች። ከቤተሰብ ጥገኝነት ነጻ መኾኗን በኩራት ትናግራለች። በዘርፉ ላይ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያግዙ ተቋማት እና ሠራተኞቻቸው አገልግሎቱን አጠናክረው እንዲሰጡም አሳስባለች።
የምዕራብ ጎጃም ዞን የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሳለአምላክ ወለላው የሰላም ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ብዙ ወጣቶች በግልም በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተውም ወደ እንስሳት ፓኬጅ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል። የገበያ ትስስሩም ጥሩ እንደነበር ገልጸዋል። እንቁላል ለብርሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ እስከማቅረብ የደረሰ ምርት እና ትስስር ተፈጥሮ እንደነበርም ገልጸዋል። ለዚህም ጽህፈት ቤታቸው ጠንካራ ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት።
ተደራጅተው ሲሰሩ ተቀራራቢ አመለካከት ያላቸውን ከማደራጀት ላይ የሚቀር ነገር ስለሚኖር ወደ ሥራ ሲገቡ የሃሳብ መከፋፈል እና ያለመስማማት ይኖራል፤ ለመፍረስም ይዳረጋሉ ያሉት አቶ ሳለአምላክ የእኛ ድጋፍ ግን ከግዴታዎቻችንም አልፈን በመሥራታችን ለውጤታማነት አብቅቶናል ብለዋል። በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ ሳይቀር ወደ እንስሳት ልማቱ በስፋት መግባቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በሰላም እጦቱ ምክንያት ወረዳዎችን ለመደገፍ ብንቸገርም ሥራ ፈጣሪዎችን ለማገዝ ባለሙያዎች ከሙያዊ ግዴታቸው በላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ እና በመመካከር ብዙ መሰናክሎችን ለማለፍ እገዛ ማድረግን እንቀጥላለን ብለዋል አቶ ሳለአምላክ።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!