
ባሕር ዳር: የካቲት 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተው ድርቅ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት በኾነው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ይገኛል። አርሶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ የዘለለ ምርት እንዳያመርቱ አድርጎ ቆይቷል። የአርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የምግብ ዋስትና ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባም አድርጎታል።
በዚህ ዓመትም በሀገሪቱ ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች የአማራ ክልል አንዱ ነው። በክልሉ በ43 ወረዳዎች ድርቅ ተከስቶ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። ሕጻናት እና እናቶች ደግሞ ይበልጥ የችግሩ ሰለባ እንደኾኑ ከሰሞኑ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከድርቁ ጋር ተያይዞ በአፋጣኝ ሥርዓተ ምግብ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ተነስቷል።
በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ከ250 ሺህ በላይ ህጻናት ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ነው የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ ሥርዓተ ምግብ የቅኝት እና ምላሽ ሰጭ ባለሙያ ኃይሌ አያሌው ያነሱት።
ባለሙያው እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ሁሉን አቀፍ የምግብ እጥረት ተጠቂዎችን የልየታ ሥራ ሠርቷል። በልየታውም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የኾኑ ህጻናት እና ነፍሰጡር እናቶች ለጤና እና ሥርዓት ምግብ ይበልጥ ተጋላጭ መኾናቸው ተገልጿል። ልየታ ከተሠራላቸው ከ1 ሚሊዮን 164 ሺህ በላይ ህጻናት ውስጥ 23 ሺህ የሚኾኑት ከፍተኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሕክምና እና አልሚ ምግብ ያገኙት 53 በመቶ ብቻ ናቸው።
ከ230 ሺህ 300 በላይ የሚኾኑት ህጻናት ደግሞ መካከለኛ አጣዳፊ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥም ድጋፍ ያገኙት 15 በመቶ ብቻ ናቸው። 130 ሺህ 977 መካከለኛ የምግብ እጥረት ያለባቸው እናቶች መለየታቸውንም ባለሙያው ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ የአልሚ ምግም ድጋፍ ያገኙት 11 በመቶ ብቻ ናቸው።
በድርቁ ከተከሰተው ሥርዓተ ምግብ ባለፈ እንደ ኩፍኝ፣ አባሰንጋ፣ ትክትክ፣ ኮሌራ የመሳሰሉ በሽታዎች ሌላኛው ችግር እንደነበር አንስተዋል። አሁንም ከችግሩ ያልተላቀቁ ወረዳዎች መኖራቸውን ነው የነገሩን።
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የተከሰተውን የሥርዓተ ምግብ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየሠራ ይገኛል።
የተደረጉት ድጋፎች ከችግሩ ስፋትና በክልሉ ከተከሰተው የሰላም ሁኔታ ጋር ተያይዞ በቂ አለመኾናቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ሌሎች ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡም ድጋፍ እንዲያደርግ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ሥርዓተ ምግብ ላይ ምርምር እና የዳሰሳ ጥናት ማድረጉንም ገልጸዋል። በቅርቡም የሥነ ምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ቤተ ሙከራ ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!