
ባሕር ዳር: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም የሁሉም ነገር መጀመሪያም መጨረሻም መኾኑን በወረታ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት የተገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን ከፎገራ ወረዳ እና ከወረታ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር በወረታ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ የተገኙት ነዋሪዎች ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም እና ልማት ነው ብለዋል። ሕዝብ ደኅንነቱን የሚጠብቅለት መንግሥት እንደሚፈልግም አንስተዋል። መንግሥት ከሕዝብ ጋር መሥራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል። መንግሥት ያለ ሕዝብ ሕዝብ ያለ መንግሥት ምንም ናቸው ብለዋል።
ገበሬው እንዲያርስ፣ ነጋዴው እንዲነግድ ዘላቂ ሰላም መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለአርሶ አደሮች የግብዓት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚገባም አንስተዋል። የማዳበሪያ አቅርቦት የወቅቱ የአርሶ አደሮች ዋና ጥያቄ መኾኑንም ተናግረዋል። መንግሥት ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል። በክልሉ ያለው ግጭት ለማንም እንደማይጠቅምም ገልጸዋል። ወንድም ወንድሙን በመግደል እና በመዝረፍ የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ሰላምን በማምጣት የተከበረውን ስማችንን መመለስ ይገባል ነው ያሉት። ግጭት ይበቃል፣ ሰላምን እናጽና ብለዋል። ባሕሪ እና ፍቅር ካላጣን በስተቀር ሀብት አላጣንም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ። ባለሃብቶች እና ነጋዴዎች ለሰላም መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል። ሰላም የሁሉ ነገር መጀመሪያም መጨረሻ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ ዘመኑን የዋጀ እና ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ለውጥ እንደሚፈልግም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ባለፈው ሥርዓት ጭቆና እና በደል ሲደርስበት መቆየቱን ያነሱት ተወያዮቹ ኩሩ እና ጀግና የኾነው ሕዝብ ያለ ክብሩ ስሙ ሲጠፋ መቆየቱንም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ የወሰን እና የማንነት፣ የሕገ መንግሥት ጥያቄዎች በዘላቂነት አለመመለስ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማንነት ብቻ የሚደርሰው ግድያ እና መፈናቀል በሕዝብ ውስጥ ቅሬታ መፍጠሩንም ገልጸዋል። የልዩ ኃይል መልሶ ማደራጀት በቂ ውይይት ሳይደረግበት መፈጸም ሌላ ችግር እና ጥርጣሬ መፍጠሩን ነው የተናገሩት። የማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ የተፈጠረው ችግር ሕዝብን ማስቀየሙንም አንስተዋል።
በሕገ ወጥ ንግድ እና በሚሠራው አሻጥር ትርፍ አምራች የኾነው ሕዝብ በኑሮ ውድነት እየተቸገረ መኾኑንም ገልጸዋል። ጀግኖችን ማክበር፣ የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ እና ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የአግልግሎት አሰጣጥን ማስተካከል እንደሚገባም አንስተዋል። ለግጭት መነሻ የሚኾኑ ጥያቄዎች መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ግጭት ሕዝብን አይጠቅምም ያሉት ነዋሪዎቹ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል። የፀጥታ ተቋምን በማጠናከር ሰላምን ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል። የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ ለመኾን እና ተወዳዳሪ ለመኾን ሰላምን ማስቀደም እንደሚገባም ገልጸዋል።
መንግሥት የመንገድ እና የንፁሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግሮችን እንዲፈታም ጠይቀዋል። መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ ሲፈታ ሕዝቡ ሰላምን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን እንደሚጠበቅል ገልጸዋል። ያለመሰልቸት ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ተደራጅተው በሚሠርቁ ኃይሎች እየተሰቃየ መኾኑንም ገልጸዋል።
ተወያዮቹ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን በመያዝ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ይጠበቃል ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶችን በቤተክህነት እና በመስጊዶች በመጥራት የታጠቁ ኃይሎችን እንዲገስጹ እና እንዲመክሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል። መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ግልፅ ምላሾችን መሥጠት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!