
ደብረ ታቦር: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ከፎገራ ወረዳ እና ከወረታ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር በወረታ ከተማ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ ተመላክቷል። ግጭት ሕዝብን እና ሀገርን በእጅጉ እንደሚጎዳም ተነስቷል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳደሪ ጥላሁን ደጀኔ የራቀውን ሰላም በራሳችን አቅም መመለስ ካልቻልን በስተቀር ስለፈለግነው ብቻ ማምጣት አይቻልም ብለዋል። ሰላም እንደ እስትንፋስ ሁሉ ውድ መኾኑንም ተናግረዋል። የሰላም እጦት የተፈጠረው በሚፈለገው ልክ ባለመሥራታችን ነው ብለዋል።
ባላስፈላጊ አካሄድ ዋጋ መክፈል እንደማይገባም ገልጸዋል። የትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ለዘላቂ ሰላም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። የአማራን መሠረታዊ ጥያቄ ለማስመለስ አማራን መግደል እንደማይገባም አስገንዝበዋል። ጥያቄ በመገዳደል አይመለስም መግባባት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በግል ፍላጎት ሰውን መግደል እና ማገት ነውር መኾኑንም አንስተዋል። ያልተገባ አሥተሳሰብ ወደ ሽብርተኝነት እና ሀገርን ወደማፍረስ እንደሚሸጋገርም ተናግረዋል። የተከበረውን ስም እና ክብር ለተራ ተግባር ማዋል አስፈላጊ አለመኾኑንም አንስተዋል። የሕዝብን ጥያቄ ሽፋን በማድረግ ሕዝብን ማንገላታት እንደማይገባም ገልጸዋል። በውስጥ ያለ ግጭት እና የሰላም እጦት በእጅ ያለን ነገር እንደሚያሳጣም ተናግረዋል።
ለአርሶአደሮች የግብዓት አቅርቦት አልቀረበም እያሉ እየከሰሱ የግብዓት አቅርቦት እንዳይሠራጭ ማድረግ እና መዝረፍ የሕዝብ ጠላትነት መኾኑንም አመላክተዋል። መንግሥት ለልማት ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዝብን ያማረረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት እንሠራለን ነው ያሉት። የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት ይጠበቅብናል ብለዋል። የአካባቢውን ፀጋ በአግባቡ ማልማት እና መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሕዝብን የሚመጥን ሥራ የሚሠራ መሪ እና ባለሙያ መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል። ችግሮችን በመደጋገፍ መፍታት ይጠበቃልም ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን መፍጠር ተቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በግጭት ውስጥ የሚኖር ማኅበረሰብ ለበርካታ ችግሮች እንደሚዳረግም አመላክተዋል። የኑሮ ውድነትን ለመግታት ሰላምን ማረጋገጥ እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የፀጥታ ኃይል ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቢያድግልኝ ሽፈራው የነበሩ ችግሮችን በተደጋጋሚ በማንሳት ብቻ የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩን ገልጸዋል። ለችግሮች መፍትሔ ማዘጋጀት እና ችግሮችን በቶሎ መቅረፍ ይገባል ብለዋል። የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ መንግሥት ለይቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። አንዳንድ ጥያቄዎች ጊዜ እና የሌሎችን እግዛ የሚጠይቁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በግጭት የሚፈታ ጥያቄ አለመኖሩንም አንስተዋል። ሕግ ካልተከበረ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ይጋለጣሉ ነው ያሉት። ችግሮችን ለአንድ አካል ብቻ መስጠት መፍትሔ እንደማይመጣም አመላክተዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባልም ብለዋል።
ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ጥያቄዎችን መፍታት ይገባል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው የውስጥ አንድነትን በመሸርሸር ለጠላት ተጋላጭ መኾን አይገባም ብለዋል። ወንድማማችነትን እና እህታማማችነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ከአንድነት ያፈነገጠ አካሄድ ለሕዝብ እንደማይጠቅምም አንስተዋል። በክልሉ በተፈጠረው ችግር የክልሉ ልማት መስተጓጎሉን፣ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ሰው ስለ ሰላም ካልሠራ በስተቀር ዘላቂ ሰላም እንደማይመጣም ገልጸዋል። የውስጥ ችግሮችን በመፍታት ወደ አንድነት መምጣት ወሳኝ መኾኑንም አመላክተዋል። የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በሕዝብ ተሳትፎ መፍታት ይገባልም ብለዋል። የቆዩ የአማራ ሕዝብ እሴቶችን በመጠቀም ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል። ሁልጊዜም ለውይይት ትልቅ ቦታ መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል። ችግሮችን የሚያባብሱ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ ይገባቸዋልም ብለዋል። መንግሥት ራሱን ገምግሞ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በሕዝብ ሰቆቃ ላይ ሃብት የሚሰበስብን አካል በቃህ ማለት ይገባልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) “ችግርን በውይይት የሚፈታ ሀገር ዘላቂ ልማት እና ሰላም ይኖረዋል” ብለዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት ብልህነት መኾኑንም ገልጸዋል። ውስጣዊ አንድነትን የሚያሳጡ አካሄዶችን መታገል ይገባል ነው ያሉት።
አስተሳሰብን ሰፋ በማድረግ ሀገር የገጠማትን ችግር መፍታት ይገባል ነው ያሉት። አማራ ጥበበኛ ነው ያሉት ኀላፊው ችግሮችን በጥበብ መፍታት ይገባል ብለዋል። ጠላት የሚሰጠንን አጀንዳ በመያዝ መደናገር አይገባንም ነው ያሉት። በሆይሆይታ ሀገር እንደማይመራም ተናግረዋል። ታላቅ ታሪክ እና ታላቅ እድል ያለውን ሕዝብ የሚመጥን ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንዳትጸና፣ ወንድማማችነት እንዳይጠናከር የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ለመፍትሔ እንኳን ግራ የገባው አካሄድን መከተል እና ለሕዝብ የማይጠቅሙ ሃሳቦችን መደገፍ እንደማይገባም አንስተዋል። ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ወገኖች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በማዳበሪያ አቅርቦት ችግር የክልሉ መንግሥት ይቅርታ ጠይቆ ለዘንድሮው በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። መንግሥት የሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያደርገው ሥራ የሕዝብን ተሳትፎ እንደሚፈልግም ተናግረዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት እንጂ ሕዝብን ለስጋት የሚጥል፣ ንብረትን የሚያወድም እና ሰውን የሚገድል ጦርነት አያዋጣም ብለዋል። ውይይትን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከግጭት አዙሪት በመውጣት ወደዘላቂ ሰላም መጓዝ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። ግጭት ችግርን የሚያሰፋ እንጂ የሚፈታ አይደለም ብለዋል። መንግሥት ለውይይት ሁልጊዜ ዝግጁ መኾኑንም አስታውቀዋል። ሰላምን እየጠበቁ የልማት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት። በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ የልማት ሥራዎች መቆማቸውንም ገልጸዋል። የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ሰላምን መገንባት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!