በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ መምህራን እና ብዛት ያላቸው የትምህርት ተቋማት ቢኖሩም የትምህርት ጥራቱ በሚጠበቀው ልክ እንዳልኾነ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

27

ጎንደር: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው የጎንደር ቀጣናን የስድስት ወራት አፈጻጸም ከቀጣናው የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር ገምግሟል። እንደ ክልል ባለፈው ስድስት ወራት የትምህርት ሥርዓቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት መስተጓጎሉን ያነሱት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የተሻለ የትምህርት አሰጣጥ እንደነበር አንሰተው የጎንደር ቀጣና ለዚህ ማሳያ እንደኾነም ገልጸዋል።

የጎንደር ቀጣና ሰላሙን አስጠብቆ የትምህርት ሥርዓቱን ከመከወን ባለፈ ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ የምገባ ሂደትቱ እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል። በጎንደር ያለውን ተሞክሮ ለሌሎች አካባቢዎች በማጋራት የክልሉ የትምህርት ሥርዓት የተሻለ እንዲኾን እንደሚሠራም ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል።

በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ መምህራን እና ብዛት ያላቸው የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ያነሱት ዶክተር ሙሉነሽ የትምህርት ጥራቱ በሚጠበቀው ልክ እንዳልኾነም ተናግረዋል። የትምህርት ዘርፉን በማሳደግ ፈጣሪ እና ተመራማሪ ትውልድ በመፍጠር ለሀገር ኢኮኖሚ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ማድረግም የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ትምህርት የዕድገት መሠረት መኾኑን ያነሱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የትምህርት ዘርፉን ለማሳደግ በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል። የትምህርት ዘርፉ ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግ ለትምህርት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላት አንዱ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም ምክትል ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ የምዕራብ ጎንደር እና የሰሜን ጎንደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊዎች በቀጣናው የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ በተገቢው መንገድ እንዲከወን መደረጉን ገልጸዋል። በምዕራብ ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሰላም እጦቱ ተጽእኖ ያሳደረባቸው ትምህርት ቤቶች ስለመኖራቸው እንዲሁም ሰሜን ጎንደር እና አካባቢው ላይ ደግሞ በዞኑ የተከሰተው ድርቅ ፈታኝ መኾኑን መምሪያ ኀላፊዎቹ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ካለንበት ውስብስብ ችግር ለመውጣት እርስ በእርስ የመከባበር፣ የመቻቻል እና የመደማመጥ ባሕላችንን ማዳበር አለብን” አቶ መልካሙ ሽባባው
Next article“ችግርን በውይይት የሚፈታ ሀገር ዘላቂ ልማት እና ሰላም ይኖረዋል” ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር)