
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቢቸና ከተማ አሥተዳደር ከእነማይ ወረዳ አሥተዳደር ጋር በመተባበር “ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጹግና” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በቢቸና ከተማ አካሂደዋል።
የውይይት መድረኩ በአካባቢው የተከሰተውን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ለመፍታት ያለመ ሲሆን የቢቸና ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ምንይችል አየለ ለውይይት መነሻ ባቀረቡት ጽሑፍ ባለፉት ወራት ያጋጠመው የፀጥታ ችግር በከተማዋ እና በማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥናቄዎች ይፈቱ፣ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ችግሮች በአፋጣኝ ምላሽ ይሰጣቸው፣ መንግሥት እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት መፍታት አለበት ብለዋል። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንግልት እያደረሱብን ነውና ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥል፣ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ መሠራት አለበት እና የአማራ ሕዝብ በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቆሶ በነፃነት የመሥራት መብቱ ሊከበር ይገባል። የአማራ ሕዝብ ፍትኃዊ የልማት ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች አንስተዋል።
የእነማይ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አዲሱ ተሻለ የተፈጠረው ችግር በማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማድረሱን ተናግረዋል።
በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት መቸገራቸውን እና ለእንግልት ስለመዳረጋቸውም ተናግረዋል።
የመንግሥት ተቋማትን እስከታች ድረስ መደበኛ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ለማድረግ መቸገራቸውን ነው የተናገሩት።
በተለይ ለቀጣዩ የምርት ዘመን እየቀረበ ያለውን ግብዓት ለአርሶ አደሮች ማድረስ እንዳልተቻለ እና ከቦታ ቦታ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ዘረፋ እየደረሰበት መኾኑን ተናግረዋል። በወረዳው ባሉ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸውን እየተሠሩ ባለመኾኑ በተማሪዎች እና በወላጆች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መኾኑን ጠቁመዋል። የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እንድንመለስ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ወይይቱን የመሩት የምስራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ መልካሙ ሽባባው የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች እንዲፈቱ መንግሥት ጥረት እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት ጠመንጃ አንስቶ እርስ በእርስ በመገዳደል ሳይኾን ሁሉም እንደየድርሻው የበኩሉን ሲወጣ መኾኑንም ገልጸዋል።
“ካለንበት ውስብስብ ችግር ለመውጣት እርስ በእርስ የመከባበር፣ የመቻቻል እና የመደማመጥ ባሕላችንን ማዳበር አለብን” ነው ያሉት አቶ መልካሙ። የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል ማኅበረሰቡ ድርሻው የጎላ ነው ያሉት አቶ መልካሙ የሃይማኖት አባቶች በየእምነት ተቋሞቻቸው እንደየአስተምህሮቶቻቸው ሰለ ሰላም መስበክ ይገባቸዋል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ንጉስ ድረስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!