ኅብረተሰቡ ለሰላም ያሳየውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ሊያረጋግጥ እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው አሳሰቡ።

20

እንጅባራ: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ”ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ”በሚል መሪ ሃሳብ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚመክር ሕዝባዊ ውይይት በቻግኒ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይበልጣል ሰይድ በክልሉ ባለፉት ወራት የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በርካታ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። የፀጥታ መዋቅሩ ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በሠራው ሥራ በከተማ አሥተዳደሩ አንጻራዊ ሰላም መኖሩንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል።

የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ዘላቂ ሰላምን ማጽናት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለውን መነሳሳት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ሕዝባዊ ውይይት በተደረገባቸው በሁሉም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት አሳይቷል ብለዋል። ሰላም በምኞት ብቻ የሚመጣ አይደለም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡ ለሰላም ያለውን ፍላጎት በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባልም ነው ያሉት። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ልጆችን ከትምህርት ገበታቸው በማፈናቀል፣ የግብርና ሥራን በማስተጓጎል እና የኅብተሰቡን ሰላም በማወክ የሚመጣ ሰላምም ኾነ ልማት አለመኖሩን ተናግረዋል።

የቻግኒ ከተማ ከአምስት ያላነሱ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች ተቻችለው እና ተከባብረው ለዘመናት በጋራ የኖሩባት ከተማ ናት ያሉት ተሳታፊዎቹ ይህም ኅብረተሰቡ ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የሚመነጭ እንደኾነም ተናግረዋል። በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጸሙ ዘረፋ እና ከፋፋይ ድርጊቶች የወቅቱ ፈተናዎች በመኾናቸው ድርጊቱ መቋጫ እንዲያገኝ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
በውይይቱ ከቻግኒ ከተማ አሥተዳደር፣ ከጓንጓ እና ከዚገም ወረዳዎች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ:-ሳሙኤል አማራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ማይካድራ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።
Next article“ካለንበት ውስብስብ ችግር ለመውጣት እርስ በእርስ የመከባበር፣ የመቻቻል እና የመደማመጥ ባሕላችንን ማዳበር አለብን” አቶ መልካሙ ሽባባው