“ፈተናዎችን ለመሻገር ለዘመናት የቆየውን የፖለቲካ አካሄድ በመቀየር የአብሮነት ባሕልን ማጠናከር ይገባል” ምክትል ርእሠ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን

18

አዲስ አበባ: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሃብት በመፍጥር ጉዞዎች ላይ ስላጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ አቅጣዎች ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው። በውይይቱ ላይ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።

በውይይቱ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የቤት አቅርቦት ችግር፣ የመሰረተ ልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ምን እንደነበሩ ተነስቷል። ከተነሱ ችግቶች ውስጥ የተፈቱ ችግሮች እና በቀጣይ በእቅድ ሊፈቱ የታሰቡ ችግሮች መኖራቸውን እና እንዴት እንደሚፈቱ የሚያግዙ ሃሳቦች ተነስተዋል። የቀጣይ አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በስኬቶች እና ጉድለቶች ላይ ሕዝባዊ ውይይት ማካሄድ ሀገርን ለመገንባት እና የመግባባት አቅምን ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል። በቀጣይም ምክክሮችን በማሳደግ ችግሮችን በአብሮነት ለመፍታት መተባበር ይገባል ብለዋል።

ለሕዝብ አስፈላጊ የኾኑ ሥራዎች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ የተሠሩ ሥራዎች በቂ ባለመኾናቸው መንግሥት በትጋት ይሠራል ብለዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ትልቁ መፍትሔ በሰላማዊ መንገድ ውይይት ማካሄድ መኾኑን ገልጸዋል።

“ፈተናዎችን ለመሻገር ለዘመናት የቆየውን የፖለቲካ አካሄድ በመቀየር የአብሮነት ባሕልን ማጠናከር ይገባል” ሲሉም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። የተሳሳተውን ትርክት በማረም ለሀገር የሚጠቅሙ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሃሳቦችን ማስረጽ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሕዝቡ ቅሬታውን በሰላማዊ መንገድ ለመንግሥት ማቅረብ አለበት፣ መንግሥትም ጥያቄዎችን በመቀበል በእቅድ ለመመለስ ይሠራል ሲሉም ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች መንግሥት እየሠራ ከሚገኘው የልማት ሥራ ጎን ለጎን የሰላም እጦቱን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ማረጋጋት እንደሚገባ ገልጸዋል። የኑሮ ውድነቱን በማስተካከል ለማኅበረሰቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሠጥም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:-ራሄል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ የድል ጉዞዎችን ለማጠናከር እና ተግዳሮቶችን በውይይት እና በትብብር ለመፍታት ያለመ ውይይት በኮረም ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next articleበምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።