“የመንግሥት ዓላማ ሕዝብን መጥቀም እና ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ነው” ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር)

20

ባሕር ዳር: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሕብረ ብሔራዊነት ወንድማማችነት እና እህታማማችነት ለዘላቂ ሰላም እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በወረታ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ ውይይት እየተደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚገጥሟትን ችግሮቿን እየፈታች የምትሄድ ገናና ሀገር መኾኗን አንስተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ነፃነቷን አስከብራ የኖረች እና እየኖረች ያለች ሀገር መኾኗንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ የምትኖር ሀገር ናትም ብለዋል። በቅርብ ጊዜ የሕልውና አደጋ በተፈጠረ ጊዜ በአንድነት እና በጀግንነት ሕልውናችን አስከብረናል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የዘመኑ መገለጫ ባልኾነ መንገድ የፀጥታ መድፈረስ ችግር ገጥሞ መቆየቱን አንስተዋል።በተፈጠረው ችግር ንብረት ወድሟል፣ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ የስነ ልቡና ጫናም ፈጥሮ ቆይቷል ነው ያሉት። የአካባቢው ማኅበረሰብ ሲንገላታ፣ አርሶ አደሮች መሳሪያቸውን ሲነጠቁ እና ሃብታቸውን ሲያጡ መቆየታቸውን አንስተዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ እና መላው የአማራ ሕዝብ መሪ እንዳይኖረው ሲሠራበት መቆየቱንም አንስተዋል። የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን በዞኑ ከ2 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም አንስተዋል። የፀጥታ መዋቅሩን ኃይል የማሰባሰብ እና የማሠልጠን ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል።

የመንግሥት የሕግ ማስከበር አቅም ከፍ እንዲል ከፍተኛ ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት ዋና አደተዳዳሪው በተሠራው ሥራም አካባቢው ወደ አንጻራዊ ሰላም በመምጣቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል። በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም መመለሳቸውንም ጠቁመዋል።

ከሕዝብ ጋር ለመቀላቀል ሥልጠና መውሰዳቸውን እና ለአካባቢው ሰላም እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። አሁንም በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላሙ እየመጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተሠሩ የፖለቲካ ሥራዎች መልካም ለውጦች መታየታቸውንም ተናግረዋል።

መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ ታላቅ ድል እና እድል ይዞ መምጣቱንም አንስተዋል። ሰላማዊ አማራጮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል። ሰላምን ለማጽናት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የጎደሉትን እየሞላን፣ በቀጣይ መፍትሔዎች ላይ በመግባባት ችግሮችን በመፍታት አስተማማኝ ሰላም መገንባት አለብን ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ሀገራችን ሰላም ያስፈልጋታል፣ ሕዝቦች በሰላም መኖር እና መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት። በክልሉ በተፈጠረው ችግር ዜጎች ሲንገላቱ፤ ሠርተው ለመብላት ሲቸገሩ መቆየታቸውን አንስተዋል። ከግጭት የሚተረፍ ነገር አለመኖሩንም ገልጸዋል። ችግር ሲመጣ ሕዝብ መምከር እና ችግሮችን መፍታት አለበት ብለዋል። መንግሥት ከሕዝብ ጋር እየመከረ የሚወስዳቸው እርምጃዎች እና መፍትሔዎች ሕዝብን የሚጠቅሙ መኾናቸውን አንስተዋል። በተወሰዱ እርምጃዎች አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩንም አንስተዋል።

“የመንግሥት ዓላማ ሕዝብን መጥቀም እና ዘላቂ ሰላምን ማምጣት ነው” ብለዋል። መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ለውይይት እጁን መዘርጋቱንም ገልጸዋል። ያለ ስጋት ሠርተን የምንገባበት ሁኔታን መፍጠር ይገባናል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ከሕዝብ ጋር እየመከረ መኾኑንም ገልጸዋል። ከሕዝብ ጋር እየመከርን የቀጣይ አቅጣጫዎችን እናስቀምጣለን ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምሥጋና🙏
Next articleሀገራዊ የድል ጉዞዎችን ለማጠናከር እና ተግዳሮቶችን በውይይት እና በትብብር ለመፍታት ያለመ ውይይት በኮረም ከተማ እየተካሄደ ነው።