
ባሕር ዳር: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዛሬው የትዝብት አምዳችን በባሕር ዳር ከተማ የሚስተዋለውን የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት አሠጣጥ እንዳስሳለን፡፡
የሥራ ባህሪዬ ስለሚጋብዘኝ በቀን ከአራት ጊዜ በላይ የከተማ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን እጠቀማለሁ፡፡
አንድ ቀን ከሥራ ወጥቼ ወደ ቤቴ ለማቅናት ከገጠር መንገድ ገበያ በሚለው ታክሲ ተሳፍሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያ ሥደርስ ወረድኩ፡፡
አስፋልቱን ተሻግሬ ረዳቱ “ዓባይ አዲስ ዓለም” እያለ ከሚጣራበት ተሽከርካሪ ገብቼ ቦታ ያዝኩ፡፡ ረዳቱ ከፊት ከኋላ እየተሸከረከረ ተሳፋሪዎችን ይጣራል፡፡ ሰዓቱ 11፡30 አልፏል። በርካታ ተሳፋሪዎች ወደ ተሽከርካሪው ገቡ፡፡ ተሽከርካሪው ከመሙላት አልፎ በእግር የሚቆምበት ቦታ እስኪታጣ ድረስ ተጠቀጠቀ፡፡ ረዳቱ ግን አሁንም “ዓባይ፣ አዲስ ዓለም” እያለ ደጋግሞ ይጣራል፡፡
ተሽከርካሪው ውስጥ የገቡ ሰዎች በሙሉ ያጉረመርማሉ፡፡ ከሹፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አንድ ተሳፋሪ “ልጄ ተሳፋሪዎችን ምን ላይ ልታደርጋቸው ነው?” ብለው ረዳቱን በትህትና ጠየቁት፡፡ ረዳቱ ምላሽ ሳይሰጥ መጣራቱን ቀጠለ፡፡ ድጋሚ መኪናው እኮ ሞልቷል የት ላይ ልታደርጋቸው ነው የምትጣራ ብለው ጠየቁት፡፡ በዚህ ሰዓት መኪናው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት በር ላይ ደርሷል።
ተሳፋሪው ጎልማሳ ሊደርስ የሚችለውን የትራፊክ አደጋ ቀድመው የፈሩ ይመስላሉ ጥያቄያቸውን አላቋረጡም፡፡ የረዳቱ መልስ ግን ግራ የሚያጋባ ነው ”ምን አገባዎት ካልፈለጉ ይውረዱ” ሲል ምላሽ ሰጠ፡፡ ተሽከርካሪው ውስጥ ያለው ሁሉ የረዳቱን እና የተሳፋሪውን ጥያቄ እና መልስ በየራሱ አረዳድ ተረጎመው፡፡
አንዳንዶቹ ጠያቂው የመንግሥት አካል እንደኾኑ እና ሥልጣናቸውን ለማሳየት እንደፈለጉ፣ እሳቸው ብቻ ተዝናንተው መሄድ እንደፈለጉ፣ እሳቸው ሄደው ሌሎች በእግራቸው ሲጓዙ ለችግር ተጋልጠው እንዲቸገሩ እንዳሰቡ አድርገው የሰውዬውን ጥያቄ አጣጣሉባቸው፡፡
ሌሎቻችን ደግሞ ሰዓቱ በመምሸቱ ብቻ ነበር የምናጉረመርም፡፡ ሰውየው ረዳቱን ሊያንገራግሩ ሲሞክሩ ሾፌሩ መኪናውን በፍጥነት ከአስፋልቱ ዳር አቁሞ ዙሮ በበሩ መጣ፡፡ በሩ ተከፈተ እና “እንደ ሰርዲን ጣሳ” ተደራርበው የቆሙት ተሳፋሪዎች መውረድ ጀመሩ፡፡ የወረዱት ሰዎች ሰዎችን በመገላገል ፋንታ ጭቅጭቅ ጀመሩ፡፡ ረዳቱ ሰውየውን የሚመታበት ድንጋይ ይፈልጋል፡፡ ሾፌሩ “ለምን” ብለው የጠየቁትን ሰውዬ ለመደብደብ ይገለገላል፡፡
ከረዳቱ ጋር የወረደው ተሳፋሪ ለመገላገል ጥረት ቢያደርግም ረዳቱ እና ሾፌሩ በጋራ ሰውየውን ማጥቃት ሲጀምሩ ሌሎች ሰዎች መገላገል ገቡ እና ጠቡ በረደ፡፡
ሰውየው በግምት እድሜያቸው 55 ተሻግሯል፡፡ ረዳቱ 20፣ ሾፌሩ ደግሞ 30 ዓመትን ይሻገራሉ፡፡ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለን ሰው ለመደብደብ ከተጋበዙት ረዳቱ እና አሽከርካሪው ባሻገር ተሽከርካሪው ውስጥ ኾነው ሰውየውን ለመኮነን የሞከሩት ሰዎችም አልጠፉም። የረዳቱን የገንዘብ ማጋበስ ሳይኾን መኪናው መጫን ቢያቆም ሊከሰት የሚችለውን የትራንስፖርት ችግር አንስተው ትንታኔ የሚሠጡም ነበሩ፡፡
ሌሎች ደግሞ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ሳያዋጣቸው ለተሳፋሪው ብለው እንደሚሠሩ ማብራሪያ ይሠጣሉ፡፡ ማብራሪያው ከሁሉም አቅጣጫ መጉረፍ ጀመረ፡፡
ትራፊክ ፖሊሶች በአካባቢው ስለሌሉ ተሳፋሪዎች ሰዎችን በአካባቢው ለሚገኙ የመንግሥት አካላት አስረክበው ሾፌሩ ተሳፋሪዎችን አድርሶ እንዲመለስ ተወስኖ መንገድ ተጀመረ፡፡ እድሜው አርባዎቹን የተጠጋው እና ከአሽከርካሪው በቀኝ በኩል የተቀመጠው ተሳፋሪ ማብራሪያውን አላቋረጠም። ሌሎችም በተገነዘቡበት ልክ የመሰላቸውን ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ የተፈጠረው ነገር ትዝብቴን ተመልሼ እንዳውጠነጥነው ጋበዘኝ፡፡
ለመኾኑ የባሕር ዳር ከተማን የትራንስፖርት የአገልግሎት መስጫ ዋጋ እና የተሽከርካሪውን የመጫን አቅም የሚቆጣጠረው ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ለራሴ ጠየቅሁ፡፡ እናንተስ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ?
ለመኾኑ አገልግሎት እየሠጡ ያሉ ተሽከርካሪዎች መንግሥት ባስቀመጠላቸው ዋጋ እና መጠን ነው አገልግሎት እየሠጡ ያሉ የሚለው ጥያቄ ሌላው ነው።
12 ሰው እንዲጭን የተወሰነለት ተሽከርካሪ 20 ሰው ካልጫነ እንደማይንቀሳቀስ በየቀኑ የምመለከተው ትዕይንት ነው፡፡
ውስጥ የጫናቸውን ሰዎች ደኅንነት ሳያውቅ መንገድ ላይ ሰዎች ስለቆሙ ብቻ መኪናው እንዲቆም ምልክት የሚሠጠውን ረዳት እና መኪናውን ደርድሮ የሚያቆመውን አሽከርካሪ በዓይነ ህሊናየ ቆጠርኩ፡፡ ብዙዎች ስለሚሠበሥቡት ገንዘብ እንጂ የሰዎች ደኅንነት ጉዳያቸው አይደለም፡፡
ለምን ብሎ የሚጠይቅ ሲመጣ ከአሽከርካሪው፣ ከረዳቱ እና ከተሳፋሪዎች የሚሠጠው ትችት የትየለሌ ነው፡፡ መስማት የሚችል ጆሮ ለመኖሩም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሲፈርዱብንም ሲፈርዱልንም የማንገነዘብ ሰዎች መኾናችንን ሁልጊዜ ያሳዝነኛል፡፡ መብታችንን ከምንጠይቅ ይልቅ ለሌሎች ጥብቅና መቆም ይቀናናል፡፡ እነዚህ አሠራሮች እግር ሰድደው መመለሻቸው አስቸጋሪ መኾኑን ማሰብ ግድ ይላል፡፡
እግር የጣለው የትራፊክ ፖሊስ ለምን ትርፍ ጫንክ ብሎ መጠየቅ ሲጀምር “ዓመትባል ደርሷል እንዴ?” ብሎ የሚሳለቀው ብዙ ነው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች የቁጥጥር ሁኔታ አልፎ አልፎ በመኾኑ ሰው በሰው ላይ ተቀምጦ እንድንጓዝ ተገድደናል። መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመው የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጡትን ትራፊክ ፖሊሶች ሳይጨምር፡፡ በሌሎች ቀናት ላይ ትራፊክ ተቆጣጣሪው የተሽከርካሪውን የመጫን እቅም ወይም የሚጭንበትን ዋጋ ሲጠይቅ ሰምቼ አላውቅም፡፡
አንዳንድ ተሳፋሪዎች ተሽከርካሪው ሳይሞላ ወደኋላ ሂዶ ላለመቀመጥ ቀድመው ሦስተኛ ይቀመጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ መኪናው ሞልቶ እንዲሄድ ለሌሎች ተሳፋሪዎች ወንበር ያጋራሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ በሞላ ተሽከርካሪ ውስጥ ለመሳፈር ሲታገሉ ማየት የዘወትር ትዝብቴ ነው፡፡ እናንተስ?
ሌሎች ደግሞ ረዳቱ ሦስተኛ ተቀመጡ ሥላለ ብቻ መብታችን መሥሎን የተቀመጠውን ሰው “ጠጋ በል” ብለን የምንገላምጥ እንዳለንም መታዘብ ችያለሁ፡፡
ሰዓቱ እየመሸ ሲሄድ ተደራርቦ መጫኑ መጠኑ ይጨምራል፡፡ ሰዓቱ ከመሸ በኋላ ለመንቀሳቀስ የፈለገ ሰው ተጨማሪ ሂሳብ ስለመያዙ እርግጠኛ መኾን ይኖርበታል። ከገበያ ዓባይ በሚንቀሳቀሰው ተሽከርካሪ”ቅርብ ወራጅ አስር ብር ነው” ሲል ከገበያ ገጠር መንገድ የሚሄደው ደግሞ “ሂሳብ አስር ብር ነው” ይላል እራሱ ባወጣው ተመን መኾኑ ነው።
ማታ ማታ ሹልክ ብለው መጥተው አገልግሎት የሚሠጡ ተሽከርካሪዎች ከመቀመጫ ወንበሩ በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሰው ቆሞ እንዲሄድ ሲፈርዱበት ማየትም የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች መቆሚያ እንጂ መያዣ ሥለሌላቸው ከወዲያ ወዲህ ከወንበር ጋር እየተጋጩ መሄድ የተለመደ ተግባር ኾኗል።
በወንበር ልክ ተቀምጨ የሄድኩበትን ቀን በዓይነ ህሊናየ አሰብኩ፤ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ቅርብ ወራጅ ነኝ ብሎ ፊት ላይ በኩርሲ የተቀመጠ ሰው ባልሳሳት በትንሹ ስድስት ጊዜ ለመውረድ ይገደዳል፡፡ ያም ቢኾን ተሳፋሪዎቹ ሩቅ ተጓዥ ከኾኑ ነው፡፡
ሲወርድ ሲሳፈር መንታፊ ሌቦች በኪሱ የያዘውን ሞባይል እና ገንዘብ ሳይወስዱበት ቤቱ ከገባ ተመስገን ነው፡፡ በዚህ ፈተና ውስጥ ኾኖ መንገድ ላይ ሲወርድ ሙሉ ሂሳብ እንዲከፍል ይጠየቃል፡፡ አንዳንድ ረዳቶች ከዓባይ ማዶ ጊዮርጊስ ድረስም ይምጣ፣ ከጊዮርጊስ ተሳፍሮ ዲፖ ይውረድ ሳንቲም የለኝም በሚል ሰበብ ተመላሽ ሳንቲሙን አይሰጡትም ይህም የዘወትር ተግባራቸው ከኾነ ውሎ አደረ፡፡
መልስ በተደጋጋሚ እንዲሠጥ የጠየቀ ተሳፋሪ “ሚሊዮን ብር ያበደረኝ አይመስልም” ተብሎ መዘለፍ አይቀርለትም፡፡
12 ሰው የሚጭነው ተሸከርካሪ 19 ሰው ጭኖ 20 ካልሞላ አልንቀሳቀስም ብሎ በሙቀቱ የተነሳ በሽተኞች፣ ሕጻናት እና ነፍሰ ጡር ሴቶች ሲጨነቁ ማየት የተለመደ እና በየደቂቃው የሚደረግ ትዕይንት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሦስተኛ አላስቀምጥም ሲሉ የሚደርስባቸው ዘለፋስ ታዝባችሁ ታውቃላችሁ?
አንዳንዴ ደግሞ ሦስት ኾኖ ተቀምጦ መልስ ሲጠይቅ የሚደርሰውን ግልምጫ እና “ደሃ” የሚለውን ስድብ የሚሠማው ብዙ ነው፡፡
ነፍሰ ጡር እና ልጅ ያዘሉ እናቶች በተቀመጡበት ወንበር ጠጋ ብላችሁ አስቀምጡ የሚባሉት እና አምባጓሮ የሚያስነሱ ረዳቶች ብዙ ናቸው፡፡
መሸት ሲል “ቅርብ ወራጅ አስር ብር ነው” የሚለው ማስታወቂያ በረጅሙ ይለቀቃል፡፡ አሻፈረኝ ብሎ መብቱን የጠየቀ ደግሞ ብዙ ውርጅብኝ ይደርስበታል፡፡ ተሳፋሪው በሚነሳው ጭቅጭቅ ጊዜውን ላለማስበላት፤ ረዳቱ ያሰባት ሳንቲም እንዳትቀርበት፣ ሾፌሩ ለምን ተነካሁ በሚል በተሳፋሪው ላይ ውርጅብኝ ያወርዳሉ፡፡ የሚመጣውን ችግር ቀድሞ የተነበየ ሌላ ተሳፋሪ እባካችሁ ሳንቲሙ ይቅርባችሁ እና በሰላም እንድረስ ብሎ ይማጸናል፡፡
አንድ ቀን በጀርባዋ አዝላ እና ሌላ ሕጻን በእጇ የያዘች ሴት ከሼፌሩ ጀርባ ተቀምጣለች። ረዳቱ ገና ሲያያት ለሕጻኗ ትከፍያለሽ ሲል ማሳሰቢያ ሰጠ። ልጄን አቅፋታለሁ መጫን ትችላለህ ስትል መልስ ሰጠች። “እንዴት” የሁሉም ሰው ጥያቄ ነበር። ሂሳብ መሠብሠብ ሲጀመር ረዳቱ የሰጠችውን ብር አልቀበልም የአንድ ሰው ጨምሪ ይላታል ። ሁሉም ተሳፋሪ በአንድ ድምጽ ወንበሩ እኮ የሁለት ሰው እንጅ ለሦስት አልተሠራም ብሎ ይጠይቃል። ረዳቱ ስትገባ ነግሬያታለሁ ያኔ መውረድ ትችል ነበር ሲል መለሰ። ሁሉም እጁን ከአፉ ላይ ጭኖ ዝም አለ የጠየቀ የለም፡፡ ሴትዮዋም መጫን ትችላለህ ነው ያልኩህ እንጅ እከፍላለሁ አላልኩም ብላ ዝም አለችው፡፡
በዚህ ሰበብ ከሴትዮዋ ጋር ማውራት ጀመርን። ሁሌም እንደሚያመናጭቋት እና አንዳንዶችም ቦታ የለም ብለው በመጨረሻ እንደማያሳፍሯት ነገረችኝ። የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቻችን ገመና ብዙ ነው። ከሁሉ በላይ ግን የተሳፋሪው ዝምታ እጅጉን ይገርመኛል። እናንተስ በዚህ ጉዳይ ምን ታዝባችሁ ይኾን
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!