
ደባርቅ፡ የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ከተጀመሩ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች መካከል የበለስ-መካነ ብርሃን አስፋልት መንገድ ሥራ ተጠቃሽ ነው። የዚህ አስፋልት መንገድ አካል የኾነው እና 160 ሜትር የሚረዝመው የበለገዝ ወንዝ ድልድይ ሥራ ተጠናቅቋል። ድልድዩ 18.5 ሜትር ከፍታ ያላቸው 12 ተሸካሚ ምሰሶዎች አሉት።
በጥር ወር 2015 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ተግባር በአንድ ዓመት እንደተጠናቀቀ የበለስ መካነ ብርሃን መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ተስፋ ዘለቀ ተናግረዋል።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሰለሞን ደመቀ በበኩላቸው የተለያዩ ችግሮች ባሉበት በዚህ ወቅት ለማኅበረሰቡ ችግር ፈቺ የኾነ የድልድይ ግንባታ ሠርተው ማጠናቀቅ በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የአካባቢውን ሰላም ጠብቀው ሠራተኞች ያለስጋት የአስፋልት መንገዱን እንዲሠሩ፣ ድልድዩም በአጭር ጊዜ ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ በማድረጋቸው ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የበለገዝ ወንዝ የጃናሞራ እና የደባርቅ ወረዳ ከፍሎ የሚፈስ ወንዝ መኾኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ ቀደም ድልድይ ባለመሠራቱ በክረምት ወራት ወንዙ ሲሞላ በአካባቢው የሚገኙት የደባርቅ እና ጃናሞራ ወረዳ ነዋሪዎች ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ግንኙነቶች ይቋረጥ ነበር ብለዋል። የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደተቋማት ለመሄድ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ የተሠራው ድልድይ የነበሩ ችግሮችን የሚቀርፍ እና ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ነው ብለዋል።
በማጠናቀቂያ መርሐ ግብሩ የመከላከያ ኮንስትራክሽን፣ የሰሜን ጎንደር ዞን እና የሁለቱ ወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ :-አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!