
ባሕር ዳር: የካቲት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአንበሳ ማስታወቂያ ባለቤት እና የዘርፉ ግንባር ቀደም ሰው ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ በሀገራዊ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልነት፣ በቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኀላፊነት እንዲኹም በቀይ መስቀል እና ደም ባንክ አምባሳደርነት አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ፈርቀዳጅ ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ ለእንግድነት ከተጠሩ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት የተዋበ ነጭ ልብስ ያዘወትራሉ፤ ከዚያም አጠር ካለው ቁመናቸው ጋር የሚሄድ ካባ በላዩ ላይ ይደርቡበታል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የማስተወቂያ ሥራዎች የእርሳቸው አሻራ አርፎባቸዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎችን ሠርተዋል። ለዛ ባለው እና በሚያስገመግመው ድምጻቸው ይታወቃሉ። ለወጣት የማስታወቂያ ባለሙያዎች ዓርአያ በመኾናቸውም ብዙዎች ያከብሯቸዋል።
ጋሽ ውብሸት ወርቅአለማሁ የተወለዱት መንዝ በቀድሞው ይፋት አውራጃ ማፉድ ገበያ አንቃውኃ በተባለ አካባቢ በ1934 ዓ.ም ነው። በቤተክህነት የቅስና፣ ዳዊት መድገም እንዲኹም ዜማን ተምረዋል።
ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ ዲያቆን እያሉ ግን አንድ ቀን በተወለዱበት አካባቢ ማፉድ ገበያ ያለው ክንውን ቀልባቸውን ይስበዋል። የገበያው ትርምስ፣ የሸማች እና ሻጭ አለመገናኘት በአጠቃላይ የቀያቸው ንግድ ቀልባቸውን ቢስበው አንድ መላ ይዘይዳሉ።
ረጅም ሰው በረዳትነት በማቆም ገዢና ሻጩን እያገናኙ ገንዘብ እንደሚያገኙ በማሰብ ሥራቸውን ጀመሩት። አብሯቸው የሚሠራው ደግሞ ሁለት ሜትር ከአስር ሳንቲሜትር ርዝመት ያለው ቁመተ መለሎ ሰው ነበር። በዚህ ሳምንት ታዲያ በማፉድ ገበያ ጠዋት ረጅሙ ሰው ትከሻ ላይ ወጥተው «ይህን ያህል ሰንጋ፣ ይህን ያህል ጤፍ፣ ሁሉም በየዓይነቱ ገብቷል» በማለት የመጀመሪያውን ማስታወቂያ በአየር ላይ አዋሉ። በማስታወቂያው የተሳበው ሸማች የትነው ያለው እያለ ከሻጭ ጋር እየተገናኘ ግብይቱ ሲጧጧፍ ዋለ። በዚህም የማስታወቂያ ሥራ ጽንስን ጀምረዋል፡፡
አያታቸው እና አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ግን «እንዴት የጨዋ ልጅ በገበያ መሃል ይጮሃል» እያሉ የማስታወቂያ ሥራቸውን እንዲተዉው መገሰጻቸው አልቀረም ነበር። እርሳቸው ግን ሥራውን ከማቆም ይልቅ ይበልጥ ገፍተውበታል።
ብዙም ሳይቆዩ ሰው ትክሻ ላይ ወጥተው ማስታወቂያ ከመሥራት ይልቅ ወደ ጽሑፍ ማስታወቂያ ተሸጋገሩ፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተጉዘውም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተስፋ ኮከብ ከተባለ ትምህርት ቤት የጀመሩት አቶ ውብሸት ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን ሙዚቃ እና ቴአትርም ተምረዋል።
በወቅቱ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሐረርጌ የሀገር ፍቅር ቴአትር ስላቋቋመ አቶ ውብሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ ለሁለት ዓመት ያክል በድሮው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ፍቅር ቴያትር ጭሮ፣ ገለምሶ፣ ኦጋዴን እና ቀብሪደሃር የመሳሰሉ አካባቢዎችን በመዘዋወር በርካታ ቴአትሮችን ሠርተዋል። ከቴአትር ሥራቸው በተጓዳኝ መድረክ መሪም ነበሩ።
አቶ ውብሸት ቴአትር በሚሠሩበት ወቅት መልካቸውም ኾነ ሁለመናቸው ንጉሱን ስለሚመስል ታዳሚዎች ልክ እንደ ንጉሱ እጅ እየነሱ ሰላምታ ይሰጧቸው ነበር።
ከሀገር ውጭም ቢሆን መድረክ የሚመሩበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። አቶ ውብሸት በሥራ ቦታቸው ላይ ደረጃቸውን እያሳደጉ በቴአትር ቤቱ እስከ ምክትል ዳይሬክተር ደረጃ ደርሰው ነበር። ቴአትር ቤቱን ለቀው ሲወጡም በብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት የማስታወቂያ ባለሙያነት ተቀጥረው ሠርተዋል።
ከቴአትር ሙያቸው ጋር በተያያዘ “እኔና ሰባት ገረዶቼ፣ ማሞ መክቶት፣ 3 ለ 1፣ የጥንቆላው መዘዝ፣ ውለታ በጥፊ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ እና ባሻህ ዘመኑ” የተባሉ ድርሰቶችንም አዘጋጅተዋል። ሰባት የቴሌቪዥን እና ሁለት የመድረክ ሥራዎችንም አቅርበዋል። «የክትነሽ» የሚል ፊልም ደግሞ በአሜሪካን ስቱዲዮ አቀናብረው ለእይታ አብቅተዋል። አቶ ውብሸት በበጎ አድራጎት ሥራም የሚታወቁ ናቸው፡፡ በሥራቸውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ አሚኮም በሳምንቱን በታሪክ ዝግጅቱ እንዲህ አስታውሷቸዋል።
ምንጭ፡- የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ግለታሪክ ማስታወሻ
—–//////——-/////——-//////—–///////—-
ጀግናው የታክሲ ሹፌር ስምኦን አደፍርስ ከ1905-1929
ኢትዮጵያ ውስጥ የታክሲ ሥራ በ1928 ዓ.ም ሲጀመር አዲስ አበባ ውስጥ ስምንት ታክሲዎች ብቻ ነበሩ ይባላል። ከነዚህ ስምንቱ ታክሲዎች የአንደኛው ባለቤት ስምኦን አደፍርስ ይባላል። የያኔው ዘመናዊ ሰው መኪና ሲነዳ እንደ ብርቅ እና ተዓምር ይታይ ነበር።
ስምኦን አደፍርስ፣ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ቦምብ ሲወረውሩ የተባበራቸው ጀግና ነው። በታክሲው ይዟቸው የሄደ ልበ ሙሉ ደፋር ሰው ነው።
ስምኦን አደፍርስ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሐብሮ አውራጃ በአንጫር ወረዳ ልዩ ስሙ ጉባ ላፈቶ በሚባለው ሥፍራ በ1905 ዓ.ም ነው የተወለዱት። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በመጀመሪያ እዚያው ላፍቶ በሚገኘው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደብር ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በሕጻንነታቸው በመምጣት በልደታ ማርያም ካቴድራል እና በአሊያንስ ፍራንሴዝ ትምህርታቸውነ በሚገባ አጠናቅቀዋል። ከዚያም በታክሲ ነጂነት ሥራ ተሠማርተው ይኖሩ ነበር።
ፋሽስት ኢጣሊያ ከጥንት ጀምሮ የተመኛትን ኢትዮጵያ ዳግም በ1928 ዓ.ም ወረረ። አዲስ አበባንም በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ የግፍ አገዛዙን መዘርጋት እና ማጠናከር ጀመረ። ስምኦን የእናት ሀገሩ መደፈር እና የነጮች የቅኝ ተገዥ መኾንን ያልተቀበሉ ጀግና ሰው ነበሩ፡፡
ስምኦን አደፍርስ ጣሊያንንም በጣም ስለሚጠሉ ለሀገራቸውም በጣም ተቆርቋሪ እና ታማኝ ኢትዮጵያዊ መኾናቸውን ስላወቁ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ባልንጀራቸው እንዲኾኗቸው ፈለጉ። ብዙ ከተቀራረቡ በኋላ የሆዳቸውን ምሥጢር ገለጹላቸው። እሳቸውም የእነሱን ሃሳብ የራሳቸው በማድረግ ሦስቱም እቅድ ያወጡ ጀመር። በመጀመሪያ ለማንም ሳይናገሩ በመኪናው ኾነው ወደ ዝቋላ ሔዱ። እዚያም ለ15 ቀናት ያህል ተቀምጠው በግራዚያኒ ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱ እና ከወሰዱም በኋላ ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ከረሙ። በተለይም የቦምብ መጣል ልምምድ ሲያደርጉ ሰነበቱ።
ብዙም ሳይቆዩ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ደረሰ። የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤተ መንግሥት እንዲገኝ ታዘዘ። ግቢው ዙሪያውን መትረየስ ተጠምዶበት ይጠበቅ ነበር። ግራዚያንም ለድሆች ምፅዋት እሰጣለሁ ስላለ ብዙ ሰው ወደ ግቢው አመራ። አብርሃ እና ሞገስም መኪናቸውን ቤንዚን ሞልተው ያው እንደተባባልነው መኪናዋን አዙረው ፊት በር በደንብ ይጠብቁን ብለው ስምኦንን ቀጠሯቸው። እነርሱ አስተርጓሚዎች ስለነበሩ ግቢ ገቡ። ስምኦንም መኪናቸውን አዘጋጅተው በተባባሉበት ቦታ ይጠብቃቸው ነበር።
ወደ 5 ሰዓት ገደማ ግራዚያኒ ሕዝብ ሰብስቦ ይደነፋል። የአርበኞቻችንን ስም እየጠራ ያንኳስሳል። የሁሉንም አንገት ቆርጬ ሮማ እልካለሁ ይላል። እነአብርሃ ቦምብ ጣሉበት። እርሱን እና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ጀኔራሎች አቆሰሉ። የአውሮኘላን አብራሪዎች ጀኔራል ሞተ። ከዚያም በተፈጠረው ረብሻ መትረየስ እና ጠመንጃ ሲተኮስ እነርሱ በፊት በር በኩል ሹልክ ብለው ወጥተው በተዘጋጀችው የስምኦን መኪና ወደፍቼ ተነሥተው ሔዱ። ስምኦንም እነርሱን እዚያ አድርሶ ወደ አዲሰ አበባ ተመለሰ።
የካቲት 19 ቀን በሳምንቱ ጣሊያኖች በጥቆማ መጥተው ስምኦን እና የቤት ሠራተኛውን ያዟቸው። ለብቻ አሠሯቸው። እንዲህ እንዲህ ያሉ ሰዎች ይመጡ ነበር ወይ እያሉ ሠራተኛውን ጠየቁት። እሱም ያየውን ሁሉ ነገራቸው። ፈትተው ለቀቁት። ሠራተኛው ባደረገው ጥቆማ ብዙ የስምኦን ጓደኞች ታደኑ። ታሥረውም ተገደሉ።
ስምኦን የመጀመሪያው የጭካኔ ቅጣት ከደረሰባቸው በኋላ ደጃች ውቤ ሰፈር አጠገብ በነበረው ወህኒ ቤት አሠሯቸው። አሠቃዮቹም ከእርሱ ምንም ማግኘት ስላልተቻላቸው ሚያዝያ 29 ቀን 1929 ገደሏቸው፤ እርሳቻም በጀግንነት አረፉ። አሚኮ በሳምንቱ በታሪክ ዝግጅቱ እኒህን ሀገር ወዳድ አርበኛ እንዲህ አስታወሳቸው።
ምንጭ ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሐምሌ 18 ቀን 1977 ዓ.ም “ምን ሠርተው ታወቁ” በተባለ አምድ ስር “ስምዖን አደፍርስ /1905-1929/ አርበኛው ታክሲ ነጂ”
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!