
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአምራች ኢንዱስትሪ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ፎረም “የዩንቨርሲቲ ኢንዱስትሪ እና የመንግሥት የሦስትዮሽ ትብብር ለፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ልማት አንቀሳቃሽ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ የካይዘን ልህቀት ማዕከል ተካሄዷል።
ፎረሙን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጋራ አዘጋጅተውታል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓት እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ እና የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ.ር)፣ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የግብዓት እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ ሚኒስቴሩ የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም ለማጎልበት እና የሥራ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይልን ለማፍራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት የሚቻለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናት እና ምርምር ሥራዎች የማኅበረሰቡን ችግር በሚፈለገው ልክ መፍታት ሲችሉ ነው ብለዋል።
ለዚህም የትምህርት ተቋማቱ በአምራች ኢንዱስትሪው አቅም የማሳደግ ሥራ ላይ ገቢራዊ የሚሆኑ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተለይም ሀገር በቀል የፈጠራ ሥራዎችን በማሳደግ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ሽግግርን ማፋጠን ላይ አበክረው እንዲሠሩም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠየቁት።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአምራች ኢንዱስትሪን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከመንግሥት እና ከኢንዱስትሪ አምራቾች ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ከዚህ አኳያ ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባሻገር በኢንዱስትሪዎች ገብተው የተግባር ትምህርቱን እንዲያገኙ እና የሥራ ባሕሉን እንዲለምዱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በፎረሙ ላይ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርት እና ምርታማነት የተመለከቱ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በተጨማሪም ከፎረሙ ጎን ለጎን የአምራች ኢንዱስትሪውን ሥራዎች የሚያሳይ አውደ ርዕይ ተካሄዷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!