
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ፣ የቅርስና የትምህርት ማዕከል የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ሮቢ ዋከርን የማዕከሉ የጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል፡፡
አቶ ጸጋዬ ጨማን ደግሞ የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ መርጧል።
ማዕከሉ ዛሬ የቀጣይ የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብን ይፋ አድርጓል። በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ ጠቅላላ ጉባኤውምን አካሂዷል።
ኢቢሲ እንደዘገበው፤ በዚህም ማዕከሉ የዓለም አቀፍ ጥቁሮች ንቅናቄ ማህበር መሥራች በመባል የሚታወቁትን ማርከስ ጋርቬ ልጅ፣ ጁሊየስ ጋርቬን (ዶ.ር) ደግሞ የበላይ ጠባቂ አድርጎ መርጧል።
ማዕከሉ የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ ቅርስ እና ትምህርት መሰረት ያደረገ ሥራ የሚያከናውን ይሆናል። ደረጃውን የጠበቀ የምርምር ማዕከልን የማቋቋም እና የተሻለ የትምህርት ስርዓት በመፍጠር በራሱ መተማመ የሚችል ወጣት እንዲፈጠር የሚሠራ ይሆናል ተብሏል።
የዓለም የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል የጥቁር ህዝቦችን ታሪክ፣ ባህልና ቅርሶችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ጠብቆ ለማቆየት የተቋቋመ ማዕከል ነው።
ማዕከሉ የተመሠረተው አዲስ አበባ ሲሆን መቀመጫውንም በአዲስ አበባ አድርጓል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!