
አዲስ አበባ: የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተከዜ አዳኝ ትውልድ መጽሐፍ በአዲስ አበባ ተመርቋል።
የታሪክ ቋጠሮ ግማድ፣ የባህል መቀነት፣ የቅርስ መካን እና የፖለቲካ ስበት ማዕከሏ የተከዜዋ ጠርዝ ወልቃይት የጀግኖች ታጋዮችን ብቻም ሳይኾን የጸሐፍት እና የጠቢባኑንም ቀልብ እና ልብ ስባለች።
በርካቶች አዜሙላት፣ አቅራሩላት፣ ጥቂት የማይባሉ ክቡር አካል እና ሕይወታቸውን ገበሩላት።
ወልቃይት ከሰው ልጆች በላይ መሰንቆ እና ክራር በልጅግ እና መውዜርም ተነጋግረውባታል። የሀገራት እና የተቋማት መሪዎችም መክረውባታል።
ስለ ነፃነት እና ፍትህ፣ ስለ ግፉዓን ድምጽም በርካቶች መራር ትግል እና መስዋዕትነት ተከፍሏል።
ይህን የዘመናት የጋለ ፖለቲካ ትኩሳትና የዜጎችን መብትና ነፃነት የማረጋገጥ ሂደት እና ከትናንት ተነስቶ ዛሬን የሚቃኝ እና የቀጣናውን የነገ ኹነት የሚተነትን “የተከዜው አዳኝ ትውልድ” የተሰኘ መፅሀፍ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው ተድላ ተጽፎ ለህትመት በቅቷል።
መጽሐፉ በትናንትናው እለት በባሕር ዳር ከተማ የተመረቀ ቢኾንም በዛሬው እለት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ እየተመረቀ ነው።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር ዓባይ፣ የቀድሞው የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀንበር (ዶ.ር) እንዲኹም ታላላቅ ጸሐፍት እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመውበታል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር ዓባይ መጽሐፉ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ማምጣት የሚችል መጽሐፍ ነው ብለዋል።
የመጽሐፉ ደራሲ አቶ አሸተ ደምለው ያኔ በጦርነት መኻከል ወልቃይት ስመደብ ልቤ በደስታ ተሞልቶ ነበር ብለዋል።
የወልቃይት ሕዝብ ብቸኛ ጥያቄ “አማራ ነን” የሚል ነው ያሉት አቶ አሸተ ለም መሬታችንን እና የውኃ ሃብታችንን በመፈለግ ለደረሰብን የዘመናት ግፍ እና መከራ ለመታገል በተመደብኩበት ወቅት ልቤ በደስታ ተሞልቶ ነበር ብለዋል።
የአማራና የትግራይ ህዝብ ግንኙነት እና አብሮነት ለዘመናት እንደነበረው አኹንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ወልቃይት ጠገዴም “ወልቃይት የኢትዮጵያ አንገት ናት” ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሔለን ሃፍቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!