
የመሬት አጠቃቀም እቅድን በአግባቡ በመፈጸም በመሬት ሃብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ እንደሚገባ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አሳሰበ።
ባሕር ዳር: የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመሬት አጠቃቀም እቅድን በአግባቡ በመፈጸም በመሬት ሃብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ እንደሚገባ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አሳስቧል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በሁለት ቀጣናዎች በተደረገ ጥናት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በልህቀት ዲዛይን ኮርፖሬሽን የመሬት አጠቃቀም እና የአከባቢ ተጽዕኖ ጥናት ቡድን መሪ አስቻለው ካሴ ጥናቱ መሬትን በአቅሙ እና ውጤት በሚያስገኝ መልኩ ለመጠቀም እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በክልሉ ያለው መሬት ያለበትን የአጠቃቀም ችግር ለይቶ በአግባቡ ለመጠቀም ቅድሚያ ችግሩ እና ጸጋውን ለመለየት እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
“ጥናት ግብ አይኾንም” ያሉት ቡድን መሪው ጥናቱን መሬት ላይ በማውረድ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ስለመኾኑ አንስተዋል።
የደቡብ ምዕራብ እና የማዕከላዊ አማራ ቀጣናዎች አብዛኛው የመሬት አቀማመጣቸው ወጣገባ በመኾኑ የተጎዱ ናቸው። ስለዚህ አጠቃቀምን ማሻሻል ይጠበቃል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ልማዳዊ የኾነውን የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት በመተው በታቀደ እና በተጠና መንገድ መሬቱን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥናቱ አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል።
የአሁኑ ጥናት ካሁን በፊት በመሬት ቢሮ ደረጃ ይጠና ከነበረው ጥናት የተለየ ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊው መሬቱን ለኢንቨስትመንት፣ ለመስኖ እና ለሌሎች አገልግሎቶች በውጤታማነት ለመጠቀም እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
መሬትን ለላቀ ዓላማ እና ለላቀ ምርታማነት ለመጠቀም አሁን የተደረገው ጥናት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ጥናቱ በስድስቱ የልማት ኮሪደሮች የተካሄደ ሲኾን ዛሬ የደቡብ ምዕራብ እና የማዕከላዊ አማራ የልማት ቀጣናዎች ብቻ የቀረበ እንደኾነ ጠቁመዋል።
ፕላን እና ልማት ቢሮ ጥናቱን መሠረት አድርጎ የተገኙ ውጤቶች የእቅድ አካል እንዲኾኑ ክትትል እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
መሬት ለታለመለት ዓላማ እና ለላቀ ጥቅም እንዲውል ለማድረግ እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሶሾኦ ኢኮኖሚ ባለሙያው አማረ አምባው ጥናቱ በመሬት አጠቃቀም ላይ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን እንዳመላከተ ተናግረዋል።
በጥናቱ ምርታማነትን የሚቀንሱ እንደ አፈር መሸርሸር፣ የአፈር አሲዳማነት የመሳሰሉ ነገሮች መኖራቸውን ያመላከተ ነው ብለዋል።
አጠቃላይ የግብርናው እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንዳለበት ስለማመላከቱ ነው የተናገሩት።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ሰይፉ ሰይድ ክልሉ 178 ሚሊዮን በላይ ብር በመበጀት በስድስቱ ቀጣናዎች ማለትም የሰሜን ምዕራብ አማራ፣ የተከዜ፣ የጣና፣ የምሥራቅ አማራ፣ የደቡብ ምዕራብ እና የማዕከላዊ አማራ የልማት ቀጣናዎች ጥናት መካሄዱን ጠቁመዋል።
አራቱ ቀደም ብለው ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲኾን ሁለቱ ዛሬ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
ጥናቱ የመሬት ሃብትን በአግባቡ በመጠቀም መሬቱ ተገቢውን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም እንዲሠጥ ለማድረግ ታስቦ እንደኾነ ጠቁመዋል።
ሁሉም ቢሮዎች ጥናቱን መሠረት አድርገው በመጠቀም መሬቱ የተሻለ ጥቅም እንዲሠጥ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
መሬት ባለው የተስማሚነት ልክ መጠቀም ከተቻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ምክትል ቢሮ ኀላፊው ሁሉም ይህን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት ጠቁመዋል።
ተዳፋትነቱ ከ60 በመቶ በላይ የኾኑ አካባቢዎች ለደን መዋል ሲገባቸው ለእርሻ በመዋላቸው መሬቱን ለአፈር ክለት እየዳረጉት ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው ብለዋል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው እንዳሉት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ከአሁን በፊት የመሬት አጠቃቀም እቅድ ተሠርቶላቸው ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ ዘመናዊ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ለሁሉም ነገር አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።
የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ካለ በመሬት ላይ ለሚካሄዱ የመንገድ ግንባታዎች፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች፣ የመስኖ ግድቦች፣ የኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ ግድቦች፣ የማዕድን ፍለጋ፣ የውኃ ልማት ሥራዎች፣ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ግንባታዎች፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎች፣ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለደን እና ለቱሪዝም እና መሰል ጉዳዮች የሚያስፈልገውን መሬት በዓይነትም ኾነ በመጠን ለመለየት ያስችላል ብለዋል።
የጥናት ፕሮጀክቱ አካባቢያዊ ሁኔታን መሠረት ያደረገ ዘላቂ የልማት መሠረት ለመጣል፣ በመሬት አጠቃቀም ጉድለት ምክንያት የሚከሰተውን የምርታማነት መቀነስ እና የተፈጥሮ ሃብት መራቆት ለመከላከልም ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!