
በደቡብ ጎንደር ዞን የተመደቡ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኀይል አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል። አቀባበል ያደረጉላቸው የዞኑ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች ናቸው።
የቀድሞው የልዩ ኃይል አባላት የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል። አባላቱ በወሰዱት ሥልጠና መሰረት የሕዝብን ሰላም እንደሚያስከብሩም አስረድተዋል። ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት ሕዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።
በጫካ ውስጥ ያሉ የታጠቁ ኀይሎች ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማስከበር እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል። በወሰዱት ሥልጠና መሰረት ሕዝብን ከሕልውና አደጋ ለማውጣት በሥነልቦና ስለመዘጋጀታቸውም አስረድተዋል።
እነሱ ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀማቸው ምክንያት ሌሎችም ጓደኞቻቸው ለመግባት እየጠየቋቸው መኾናቸውንም ተናግረዋል። ሁሉም እንደሚገቡ አንጠራጠርም ነው ያሉት። የሰላም ጥሪውን በጥርጣሬ የሚያዩ አካላት ጥርጣሬያቸውን አስወግደው መምጣት ይገባቸዋልም ብለዋል። መንግሥት የሚገባቸውን አቀባበል እንዳደረገላቸውም ገልጸዋል። የክልሉን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚመልሱትም ነው የገለጹት።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ አስተማማኝ ሰላም መገንባት የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ መኾኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ሁልጊዜ የምትፈተን፣ ፈተናዎቿን በቁርጥ ቀን ልጆቿ እየተወጣች አሸናፊነትን የምታውጅ ሀገር መኾኗን አንሰትዋል። የቀድሞው የልዩ ኃይል አባላት የሕልውና አደጋ በነበረበት ጊዜ ታላቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
በተፈጠረው ችግር ያልተገባ የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም መፈጠሩን ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ተጋድሎ ክልሉ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱንም አንስተዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሁልጊዜም ሀገር በክብሯ እንድትቆይ በችግሯ ሁሉ ቀድሞ የሚደርስ የቁርጥ ቀን ልጅ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥበብ በተሞላበት መልኩ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ መሥራቱንም አንስተዋል።
የቀድሞው የልዩ ኃይል አባላትም ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም የተበደለውን ሕዝብ ለመካስ መግባታቸውንም አንስተዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ ውስጥ የቀኝ እጅ ለመኾን ስለመጡም አመሥግነዋቸዋል። “ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ሰላም ለመገንባት እና ከፊት ለመሰለፍ የመጣችሁ ጀግኖች ናችሁ” ብለዋቸዋል። ሕዝብን ከችግር ለመታደግ የመጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የጸና ዓላማ እና ውስጣዊ የሀገር ፍቅር ይዘው ግዳጃቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ102ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ወርቁ አሸናፊ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ መግባት የለባትም ብላችሁ ከጀግናው መከላከያ ጋር ኾናችሁ ሀገራችሁን ያስከበራችሁ ጀግኖች ናችሁ ብለዋቸዋል። ታሪካቸውም ተመዝግቦ የተቀመጠ ነው ብለዋል። አሁንም ሀገር ብሎም የአማራ ክልል ችግር ውስጥ ነው ብላችሁ በመምጣታችሁ ሌላ ጀግንነት ነው ብለዋቸዋል። ውሳኔያቸው እንደቀድሞው ሁሉ ሌላ ታሪክ መኾኑንም ተናግረዋል።
ጀግንነታችሁን እና የቁርጥ ቀን ልጅነታችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁም ብለዋል። የክልሉ የጸጥታ ኀይል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር እየሠራ መኾኑን የተናገሩት ኮሎኔሉ የጸጥታ ሥራውን በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት። በአንድነት ሰላም ማምጣት ይገባልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!