
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በክልሉ ርእሰ መዲና ባሕር ዳር ከሰሞኑ ተካሂዷል። ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባኤው የክልሉን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥን የውይይቱ ማዕከል አድርጎ መክሯል ተብሏል።
የምክር ቤቱን መደበኛ ጉባኤ የቀጣይ ወራት አቅጣጫ አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ በመደበኛ ጉባኤው የአስፈጻሚው አካል እቅድ አፈጻጸም በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል።
ክልሉ ካለበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በበርካታ ተቋማት የታየው የስድስት ወራት አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ ከፍላጎት እና እቅድ አንጻር ግን በቀሪ ወራት ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ አንስተዋል። የሰላም እጦቱ ያልዳሰሰው ሴክተር ባለመኖሩ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በትብብር ለመሥራት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ከክልሉ አልፎ ሀገራዊ ተፅዕኖው የጎላ ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ በምክር ቤቱ መደበኛ ሥብሠባ የፌዴራል መንግሥት ካለፈው ዓመት እጥረት ተሞክሮ ወስዶ የአፈር ማዳበሪያ ግዥን በወቅቱ መፈጸሙ በጥንካሬ ታይቷል ብለዋል።
“የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ብቻውን ግብ አይደለም፤ ለተጠቃሚው አርሶ አደር በወቅቱ መድረስ አለበት” ያሉት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ በክልሉ የነበረው የሰላም እጦት በማዳበሪያ ስርጭቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል። ምክር ቤቱም በመደበኛ ጉባኤው በክልሉ የታየውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
የገቢ አሠባሠብ፣ ቱሪዝም፣ ትምህርት እና ሌሎች አፈጻጸሞች በክልሉ ምክር ቤት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ውይይት ተደርጎባቸዋል ነው ያሉት። የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በየደረጃው እንደተስተዋሉ በምክር ቤቱ ታይቷል ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ መሪን መፍጠር እና ማጀገን የክልሉ ሕዝብ ነባር እሴት እንደኾነም ተነስቷል ነው ያሉት። ቅሬታ ያላቸው ሁሉ ቅሬታቸውን ለምክክር እንዲያቀርቡ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!