የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለ 17 ወለል ሕንፃ አስመረቀ።

27

ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለ17 ወለል የቤተ መዛግብት ሕንፃ አስመረቀ።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ደራሲያንና ሌሎች ተገኝተዋል።

ጥቅምት 23 ቀን 1936 ዓ.ም ‘የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት’ በሚል ስም የተቋቋመው አገልግሎቱ፣ አዲሱን ባለ17 ወለል የቤተ መዛግብት ሕንፃ የሚያስመርቀው በ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ጋር ነው።

በቤተ መዛግብት ክምችት ረገድ በአፍሪካ ምርጥ አምስት ቤተ መዛግብት መካከል አንዱ ለመሆን እየሰራ ያለው አገልግሎቱ፣ ዛሬ የተመረቀው ሕንፃም ለዘመናት የነበረበትን የቦታ ጥበት እንደሚቀርፍ ታምኖበታል።

አገልግሎቱ በ1936 ዓ.ም “የሕዝብ ቤተ- መጻሕፍት ወመዘከር” በሚል ስያሜ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የተቋቋመ ሲሆን የተለያዩ ስያሜዎችም ነበሩት።

ለአብነትም በ1958 ዓ.ም “ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት”፣ በ1972 “ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት መምሪያ”፤ በ1986 “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ድርጅት” የሚል ስያሜ የነበረው ሲሆን አሁን ላይ “የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት” የሚል ስያሜ ይዟል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክ የመዛግብት፣ የመፃሕፍት እና ቅርሶች ክምችቱ ግንባር ቀደም የሆነው አገልግሎቱ፣ በ80 ዓመታት ውስጥ የአይነተ ብዙ ፅሁፍ፣ የድምፅና የምስል ቅጂዎችን መያዙን ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ የሰላም አማራጮችን በስፋት ያመላከተ ነበር” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ
Next article“የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ብቻውን ግብ አይደለም፤ ለተጠቃሚው አርሶ አደር በወቅቱ መድረስ አለበት” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ