
ባሕርዳር: የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ፣ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ተካሂዷል።
የክልሉን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ አፈጻጸም አስመልክቶ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ በጽሕፈት ቤታቸው ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ከየካቲት 13 እስከ የካቲት 15/2016 ዓ.ም ተካሂዷል ያሉት አፈ ጉባኤዋ ምክር ቤቱ በጉባኤው ክልላዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል ብለዋል።
ካለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን አስከትሏል ያሉት አፈ ጉባኤ ፋንቱ “የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ የሰላም አማራጮችን በስፋት ያመላከተ ነበር” ብለዋል።
ዋና አፈ ጉባኤዋ በመግለጫቸው ሰላም እና ልማት ተነጣጥለው የሚታዩ ጉዳዮች እንዳልኾኑ በጉባኤው ትኩረት ተሰጥቶ እንደታየ ተነስቶ ምክር ቤቱ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ መኾን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቶ መክሯል ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ ሰፊ የመልማት ጥያቄ እንዳለው በምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል፤ የመልማት ጥያቄውን በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት ኾኖ እንዲሠራ የሚያስችል ውይይትም ተካሂዷል ነው ያሉት።
የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን አንስቶ እንደመከረ የገለጹት አፈ ጉባኤዋ ስኬታማ ውይይቶች፣ ሰፊ የሰላም አማራጮች እና ግልጽ የቀጣይ ጊዜያት የአሥፈጻሚው አካል አቅጣጫዎች የተቀመጡበት ነበር ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!