አንድነትን ካልጠበቅን ሀገርን ልናጸና አንችልም ሲሉ ወጣቶች ተናገሩ።

16

ደብረ ታቦር፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንድነት የሀገር መሠረት ፣ የሀገር ነፃነት መነሻ እና መድረሻ እንደኾነ ይነገራል። አንድነት ድል ያመጣል ። በዓለሙ ፊት የታፈሩ እና የተከበሩ ለማድረግ አንድነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዓድዋ የአንድነት፣ የሀገር ፍቅር ፣ የመሪነት ጥበብ እና የመደማመጥ ውጤት ነው ይባልለታል። አንድነትን ጋሻቸው ያደረጉ አባቶች ድል አምጥተዋል። በዘመናቸው የመጣባቸውን ጠላት ድል መትተዋል። ከዘመናቸው ተከትሎ ለሚመጣው ትውልድ ደግሞ ኩራትን አውርሰዋል።

ዓድዋ የነፃነት ጮራ የፈነጠቀበት፣ አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲነሱ የብርሃን መንገድ ያሳያበት ታላቅ በዓል ነው። ዓድዋ ለዚህ ዘመን ችግሮችም መፍትሔዎችን ይዞ የሚቀርብ የድል ብሥራት ነው። ዓድዋን የያዘ ሀገር እና ሕዝብ ከሀገር ፍቅር፣ አንድነት፣ ጀግንነት፣ ጽናት እና ታማኝነት ዝቅ ማለት አይቻለውምና።

የከፍታ ታሪክ የወረሰ ትውልድ የከፍታ ታሪክ መሥራት፣ ሀገሩን መውደድ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት መታገል ግድ ይለዋል። ቢቻል ልጅ ከአባቱ ልቆ መገኘት ባይኾን ግን በአባት ልክ መገኘት እና የአባትን አደራ መጠበቅ ሀገራዊ አደራና ግዴታ ነው። የዚህ ዘመን ትውልድ በዓድዋ ልክ መገኘት እና የራሱን ዘመን ዓድዋ የመሥራት አደራ አለበት። ለምን ቢሉ የዓድዋን ጀግኖች የሚወድ እና እነርሱን ያከበረ ትውልድ በአከበራቸው ጀግኖች ልክ መገኘት አለበትና።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ዓድዋ በታሪክ ከመነገር ባለፈ ለዚህ ዘመን ትውልድ የአንድነት መሠረት እና ኩራት ነው ብለዋል።

ወጣት ፈቃዴ ተገን ዓድዋ ታላቅ እሴት እና ታሪክ የያዘ ለወደፊት ትውልድ የሚሻገር በዓል ነው ብሏል። ወጣቶችም ኾነ ሌሎች ማኅበረሰብ ክፍሎች የወደፊት ጉዟቸውን ለማሳመር ከአለፉት አባቶች መማር ይገባቸዋል ነው ያለው። የቀደሙት አባቶች በመስዋዕትነት ሀገር አቅንተው የተዋበች ሀገር ማቆየታቸውን ተናግሯል።

አባቶች ሀገር ያጸኑት ምን አይነት ቅንጅት ቢኖራቸው? እንዴት ቢግባቡ ነው ? አንድነታቸውን እንዴት ቢጠብቁ ነው? የሚለውን መመርመር እና ከእነርሱ መማር ይገባናል ብሏል። ዓድዋ ሀገር እንዴት እንደቆዬች እና ነጻነቷን እንደጠበቀች ትምህርት የሚሰጥ ሕያው ምስክር መኾኑንም ገልጿል። የአሁኑ ትውልድ እንደ ቀደሙት አባቶች ሁሉ በአንድነት፣ በመተማመን እና በፍቅር ሀገሩን በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኀላፊነት እና አደራ መሸከሙንም ተናግሯል። ዓድዋ በታሰበ ቁጥር ታላቅ ስንቅ የሚያዝበት እና አደራ የሚቀበሉበት መኾኑንም አንስቷል።

አባቶች ሀገራቸውን በአንድነት፣ በፍቅር ፣ በመናበብ እና ሌሎች መልካም ነገሮችን በመያዝ የምታኮራ ሀገር ሰጥተውናል ነው ያለው። ዓድዋን መነሻ በማድረግ ታላቅ ሀገርን ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቃል ብሏል። ወጣቶች በተሰማሩበት ሁሉ ሀገርን የማጽናት አደራ አለባቸው ያለው ወጣቱ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ ፍቅርን፣ አንድነትን በማስረጽ የመልካም ነገር አርዓያ መኾን ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው። ለማንኛውም ነገር አንድነት መሠረት ነውም ብሏል።

ዓድዋ አንድነትን በመጠበቅ የመጣ ነው ያለው ወጣቱ አባቶች የተከበረች ሀገር ያስረከቡን በአንድነት በሠሩት ሥራ ነው ይላል። በዚህ ዘመን አንድነት እየተሸረሸረ መኾኑንም አንስቷል። እየተሸረሸረ ለመጣው አንድነትም ዓድዋ ትልቅ ማስተማሪያ ነው ብሏል። አንድነትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመላክቷል። አንድነትን ካልጠበቅን ሀገርን ልናጸና አንችልም ነው ያለው። የአሁኑ ትውልድ አንድነትን ማጽናት አለበት ያለው ወጣቱ መልካም ሥራዎችን እያደነቁ ሌሎች መልካም ሥራዎችን መጨመር እንደሚገባም ተናግሯል።

የአሁኑ ትውልድ ዓድዋን ካስገኙ አባቶች እና እናቶች ታላቅ ትምህርት መማር እንደሚገባውም አንስቷል። ትውልዱ ታሪኩን ማወቅ እና መመርመር ይጠበታል ነው ያለው።

ሌላኛው የከተማዋ ወጣት መለሰ ዓለሙ ዓድዋ የኢትዮጵያን የመቻቻል ፣ የአብሮነት እና የፍቅር ውጤት መኾኑን ገልጿል። ዓድዋ ኅብረብሔራዊነትን ለማስቀጠል እና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያስችልም ተናግሯል። ዓድዋ ትናትን ይዞ ለነገ መልካም ነገር እንዲቀጥል እንደሚያደርግም አመላክቷል። ወጣቶች የጋራ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጿል። ዓድዋ ለሰላም እና ለአንድነት መሠረት ነው ብሏል።

ወጣቶች ለሀገር ያለባቸውን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸውም ተናግሯል። ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የሚያዋጣው አንድነት መኾኑንም ገልጿል። ከወንድማማችነት ውጭ የሚሻል ነገር አለመኖሩንም ተናግሯል። ራስ ወዳድነት እና እኔ ብቻ ልጠቀም ማለት የሚጠቅም አለመኾኑንም ገልጿል። ዓድዋ የዚህ ዘመን መከባበር ፣ አንድነት እና ፍቅር መጠንሰሻ ሊኾን ይገባልም ብሏል።

ወጣት ግርማይ አሻግሬ ዓድዋ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቁ የጀብደኝነት ታሪክ መኾኑን ነው የገለጸው። ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የተሸነፉት ነጮች ሁሉ የመሠከሩለት ታላቅ ድል መኾኑንም ተናግሯል። ዓድዋ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የተገኘ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት የኾነ የድል በዓል መኾኑንም አንስቷል። ዓድዋ ሲነሳ ታላቅ የመሪነት ጥበብ ያሳዩትን አጼ ምኒልክን እና እቴጌ ጣይቱን ማክበር እና መዘከር ይገባል ነው ያለው። ከዓድዋ ጀግንነትን፣ ኩራትን እና ነፃነትን እንደሚማርበት የተናገረው ወጣቱ ዓድዋ ባመጣው ሞገስ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በየትኛውም የዓለም ክፍል በኩራት ይንቀሳቀሳል ብሏል።

ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካውያንም ኩራት መኾኑን ነው የተናገረው። ከዓድዋ ጀግንነትን፣ አብሮነትን፣ ትሕትናን እና ሩህሩህነትን እማርበታለሁ ነው ያለው። ወጣቶች ለሰላም ዘብ በመኾን በውይይት ለሚደረግ ትግል መዘጋጀት አለባቸው ብሏል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ወጣት ሐረገወይን ሀብቱ ዓድዋ አንድ ሕዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነት እና ነፃነት መጠበቅ ምን ያክል መስዋዕትነት እንደሚከፈል ያስተምራል ነው ያለችው። አባቶች በአንድነት እና በጽናት ሀገራቸውን እንዴት እንዳስከበሩ ዓድዋ ትምህርት ነው ብላለች። ወጣቶች ዓድዋን መሠረት በማድረግ ለሰላም ዘብ መኾን ይጠበቅባቸዋል ብላለች። ሰላምን በማስጠበቅ ለሀገር ልማት መሥራት የዚህ ዘመን ትውልድ አደራ እና ኀላፊነት መኾኑንም አንስታለች።

ትውልዱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባው የተናገረችው ሐረገወይን ጥያቄዎቹ እስኪመለሱ በትዕግሥት መጠበቅም ይገባዋል ብላለች። ጦርነትን በመተው በሰላማዊ መንገድ መታገል ይጠበቃል ነው ያለችው። ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ሰላምን መጠበቅ እንደሚገባም ተናግራለች።

ዓድዋን ከመዘከር ባለፈ የእውነት መኖር፣ የእውነት መተግበር ግድ ይላል። ዓድዋ የብዙ ነገሮች መሠረት እና ኩራት ነውና። የሚያኮራ ታሪክ ያለው ትውልድ ደግሞ የሚያኮራ ታሪክ መሥራት ግድ ይለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥበብ እና ጥቁር!
Next articleየባሕር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተደረገ ነው።