የባሕር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተደረገ ነው።

17

“የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ ማግኘት እና አብሮ ማደግ በዓለም አቀፍ ሕግም ኾነ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳይ በመኾኑ ለቀጣናዊ ትብብር እና ውህደት ገንቢ ሚና አለው” የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ከማል አብዱራሂም (ዶ.ር)

ባሕር ዳር: የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ልማት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተደረገ ነው።

መድረኩ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የህልውና እና መሠረታዊ ጥያቄ የኾነውን የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ መምህራን እና ተማሪዎች ጋር ለመወያየት ነው።

በውይይት መድረኩ ሦስት ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት ያለው ፋይዳ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንፃር የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎች በማካተት እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከታሪክ አንፃር ተገቢነትቱን አስመልክቶ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ በባሕል እና ስፓርት ሚኒስቴር የኪነ ጥበብ እና ሥነ- ጥበብ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲንን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እና ተማሪዎች ተገኝተዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ከማል አብዱራሂም (ዶ.ር) “የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ ማግኘት እና አብሮ ማደግ በዓለም አቀፍ ሕግም ኾነ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳይ በመኾኑ ለቀጣናዊ ትብብር እና ውህደት ገንቢ ሚና አለው” ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የውይይት አጀንዳ በማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ወቅቱ የሚፈልገው ጉዳይ እንደኾነም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር ኾና በጎረቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ በመኾን በዓመት ብዙ ሚሊዮን ዶላር ስታወጣ ስለመቆየቷ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ የራሷ የንግድ ኮሪደር እንዲኖራት ከአካባቢው ሀገራት ጋር ስምምነት ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ ቆይቶ በቅርብ ጊዜ ውስጥም ከሶማሌላንድ ጋር በጋራ የመጠቀም ስምምነት መፈረሙ የሚደገፍ እና የሚበረታታ ተግባር መኾኑን ጠቅሰዋል።

ይህ በመኾኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ላይ እድገት ለማምጣት፣ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመኾን እና እየገጠመ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቅረፍ እንደሚያስችል አብራርተዋል።

ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንድነትን ካልጠበቅን ሀገርን ልናጸና አንችልም ሲሉ ወጣቶች ተናገሩ።
Next article27ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በ9 ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አጸደቀ።