ጥበብ እና ጥቁር!

46

ጥበብ እና ጥቁር!

[የጥቁሮች ወር (Black History Month) – የካቲት]
👉ልዩ ጥንቅር

ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ኮሚኒስቶች የእጆቻቸውን እጅጌ ሰብስበው ለመፈክር የወጡ ሁሉ አጃኢብ ባሰኙ ረጃጅም ሰልፎች ነጻነትን እና እኩልነትን ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡ ጸሐፍት በብዕራቸው፣ አቀንቃኞች በድምጻቸው፣ ጠቢባን በጥበባቸው፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች በመክሊታቸው የተዛባውን ሥርዓተ ማኅበር ለማረቅ እልክ አስጨራሽ ተጋድሎ አካሂደዋል፡፡ ለእኩልነት እና ነጻነት ከተከፈለው መስዋዕትነት ባልተናነሰ መልኩ የተስተዋለው የጥበብ አሻራም ዘመን ተሻጋሪ የሚባል ነበር፡፡

እንደ ቼ ጉቬራ በትጥቅ፣ እንደ ቦብ ማርሌይ በማይክ፣ እንደ ኦሌ ሾይንካ በብዕር፣ እንደ ማንዴላ በእስር፣ እንደ ማልኮም ኤክስ በቅኔ፣ እንደ ኢታ ጀምስ በሾርኔ ጥበብ እና ጥበበኞች ነጻነት እና እኩልነት ይመጣ ዘንድ ውድ መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡ እጅግ በርካታ አስለቃሽ ፊልሞች፣ አንጀት የሚበሉ ግጥሞች እና ስሜትን የሚቆነጥጡ የሙዚቃ ሥራዎች የጥቁሮችን ግፍ እና በደል ማዕከል አድርገው ተሰርተዋል፡፡

የዓለም ጥቁር ሕዝቦች በሀገራቸውም ኾነ ከሀገራቸው ውጭ እንደ ሰው የማይታዩበት ዘመን ትናንት እንደ ሥርዓተ መንግሥት ቅቡል ነበር፡፡ የቆዳ ቀለም የመደብ ልዩነትን እና የገዥ ተገዥ ትርክትን የፈጠረበት ጊዜም ሩቅ አልነበረም፡፡ ጥቁር እና ነጭ በተፈጥሯቸው የሰው ልጅ ቢኾኑም የቆዳ ቀለም የፈጠረው የበላይ እና የበታች አስተሳሰብ ግን በአንድ ባቡር ውስጥ አብሮ መጓዝን የሚከለክል፣ በአንድ ወንበር መቀመጥን እንደ ወንጀል የሚያስቆጥርበት ጊዜ የቅርብ ሩቅ ትዝታ ነው፡፡

የችግሩን መክፋት፣ የበደሉን መስፋት ከሚያመላክቱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የጥቁሮች እና የነጮች በሚል የተለዩ የሃይማኖት ተቋማት መኖራቸው ነበር፡፡ ዓለማዊውን ሕይዎት ንቀው ሰማያዊውን ዓለም ናፍቀው መንፈሳዊነትን የሚሰብኩት የእምነት ተቋማት በቆዳ ቀለም ልዩነት ፍጡራንን ለይተው ሲመለከቱ ማየት አሳዛኝ ሁነት ነበር፡፡ ጽድቅ የማመን እና በጎ የመሥራት ውጤት ሳይኾን ጥቁር ወይም ነጭ ኾኖ የመፈጠር ምስጢር ተደርጎም ተሰብኳል፡፡ ጥቁሮች የጨለማው ዓለም ተምሳሌት ተደርገው ሲቀርቡ፣ ነጮች ደግሞ የመጻዒው ብሩህ ጊዜ ምሳሌዎች እና የችግሮች ሁሉ መፍትሔ እንዲኾኑ ተደርጎ ተስሏል፡፡

ከበርሊን ኮንፈረንስ ቀድሞ ከ200 ዓመታት በላይ አፍሪካዊቷ ሀገር ደቡብ አፍሪካ “አፓርታይድ” በተሰኘ የባርነት ቀንበር የመከራ ዘመንን እየተጋተች ኖራለች፡፡ ከኢትዮጵያ በስተቀር በርካቶቹ አፍሪካዊያን ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ዘመን ቀድሞም ባርነት ተጭኖባቸው ቆይተዋል፡፡ ባርነትን ለመታገል ከግለሰቦች በስተቀር እንደ ሀገር የቆመ ግን ከኢትዮጵያ በፊት አልነበረም፡፡ እውቁ የታሪክ ተመራማሪ እና ጸሐፊ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ገጸ በረከት ናት ማለታቸው ለዚህ ነበር፡፡

ከዓድዋ ድል ባሻገር የካቲት ለምን የነጻነት ወር ተብሎ ተሰየመ ብሎ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ዓድዋ የወርሃ የካቲትን የድል ብሥራት ዜና አደመቀው እንጂ ሌላም ተሻጋሪ የትግል አበርክቶዎች አሉት፡፡ ከሃሪየት ቱብማን እስከ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፣ ከማልኮም ኤክስ እስከ ሮዛ ፓርክስ እና ሌሎችም ጥቁር ፖለቲከኞችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን፣ ተራማጆችን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ትግል ለመዘከር በየዓመቱ ወርሃ የካቲት “የጥቁሮች ታሪካዊ ወር” ተደርጎ ይከበራል፡፡

በተለይም የጥቁር ሕዝቦች የእጅ ሥራ ውጤት በኾነችው አሜሪካ ከ150 ዓመታት በላይ በዘር ፖለቲካ በታመሰችው ካናዳ እና ራሳቸውን የተለየ ዝርያ ያላቸው የዓለም ሕዝቦች አድርገው ይመለከቱ በነበሩት ጀርመኖች ዘንድ የጥቁሮች ታሪካዊ ወር በተለየ መልኩ እየተከበረ ያልፋል፡፡

የጥቁሮች ታሪካዊ ወር እንዲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳቡ የቀረበው በእውቁ የታሪክ ምሁር ካርተር ጂ ውድሰን አማካኝነት እንደ ምዕራባውያኑ የዘመን ስሌት በ1926 እንደነበር ይነገራል፡፡ ሃሳቡ የቀረበበት ምክንያትም የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክን ለመዘከር እና አሜሪካ ለጥቁር አፍሪካዊያን ያላትን ክብር እንድታረጋግጥ ከማሰብ የመነጨ ነው የሚሉ አሉ፡፡

የካቲት የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ኾኖ እንዲከበር የተመረጠበት ምክንያትም በተለይም በአሜሪካ ሁለት ዓበይት ክስተቶች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ የ1863ቱ የነጻነት አዋጅ በፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን የተፈረመው በወርሃ የካቲት በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን እና አፍሪካ-አሜሪካዊው አንደበተ ርቱዕ፣ የማኅበራዊ ለውጦች አቀንቃኙ፣ ጸሐፊው፣ ተራማጁ እና ተወዳጁ ፍሬዴሪክ ዳግላስ የተወለዱበትን ወርሃ የካቲትን ለመዘከር ያለመ እንደኾነም ይነገራል፡፡

“የጥቁር ሕዝብ ታሪክ የአሜሪካም ታሪክ ነው” የሚሉ የዓለም ጥቁር ሕዝብ ሰብዓዊ መብት ታጋዮች መበራከት እና መበርታት የኋላ ኋላ እያየለ መጣ፡፡ የካርተር ጂ ውድሰን የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ክብረ በዓልም ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በኋላ በአሜሪካ ሕጋዊ እውቅና እና ሰውነት አገኘ፡፡ (እ.አ.አ) 1976 በፕሬዚዳንት ጄራልድ ፎርድ መሪነት ወርሃ የካቲት በአሜሪካ የጥቁሮች ታሪካዊ ወር መኾኑ እውቅና ተሰጠው፡፡

ላለፉት 48 ዓመታትም በዓለም ዙሪያ የካቲት የጥቁሮች ታሪካዊ ወር ኾኖ እየተከበረ ቀጥሏል፡፡ ዘንድሮም የጥቁሮች ወር መሪ ሃሳብ ጥበብ እና ጥቁር ላይ አተኩሮ “ጥበብ የእውነት መውጫ ናት፤ ጥበበኞችም የስልጣኔ አቀንቃኞች ናቸው” በሚል ሃሳብ በመላው ዓለም ይታሰባል፡፡

አስከፊው ዘርን እና የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረገው ጭቆና ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ ቢከስምም ዛሬም ድረስ የዓለም ጥቁር ሕዝብ ከዘረኝነት ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኗል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህንን ኋላቀር እሳቤ ለመታገልም ጥበብ እና ጥበበኞች ሚናቸው የጎላ ነው ተብሏል፡፡

መልኩን እየቀየረ ከስፖርት ሜዳ እስከ ፍትሕ አደባባዮች የሚስተዋለውን የጥቁር ሕዝብ ጥቃት እና የዘር ፖለቲካ ፈጽሞ ለማክሰም ጥቁሮች ጽናት ባለው ጥበብ መታገል እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ አሁንም ድረስ ጣሊያን በዘራችው የዘር ፖለቲካ ዋጋ እየከፈለች እና መከራ እያጨደች ያለችው ኢትዮጵያ ዳግም ለዘር በሽታ ፈውስ ትኾን ዘንድ ጠቢባንንም፤ ጥበብንም ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ምንጭ፡- ሂስትሪ ዶት ኮም

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ማስቀጠል እንደሚገባ ሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
Next articleአንድነትን ካልጠበቅን ሀገርን ልናጸና አንችልም ሲሉ ወጣቶች ተናገሩ።