
ባሕር ዳር፡ የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ ሰላምና አንድነትን በማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ። 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ጸጥታ የጋራ የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሀገሪቷን ሰላም በማጽናትና አንድነትን በማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ ማስቀጣል ይገበል።
ቀደም ሲል በነበሩ የተዛቡ ትርክቶች ምክንያት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በማጥበብ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ሁሉንም ዜጋ ባሳተፈ መልኩ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአንድ ሀገር እድገት እና ለውጥ መሰረቱ ሰላም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህንኑ እውን ለማድረግ መንግሥት ለሰላም ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተከናወኑት የሰላም ግንባታ ተግባራትም እንደ ሀገር ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመሩ ጥረቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሀገር አቀፉ የሰላምና የጸጥታ የጋራ የምክክር መድረክ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና ክፍተቶችን በማረም በዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጅሉ በበኩላቸው የጋራ ችግሮቻችን በጋራ የመፍታት ባሕላችንን በማጠናከር እንደ ሀገር የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጽጥታ ችግሮች የሕዝቡን የልማት ጥያቄ በወቅቱ ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት እየሆኑ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ጥረት አየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ጸጥታ የጋራ የምክክር መድረክ በክልሉ መዘጋጀቱ መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የጋራ የምክክር ያለፈው ግማሽ ዓመት የተጠቃለለ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና በቀጣይ የተከለሰ ዕቅድ ዙሪያ እንደሚመክር ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ የሁሉም ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አሥተዳደሮች የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮች እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!