“የጸጥታ ሁኔታው የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል” የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር

17

ደብረ ታቦር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጸጥታ ችግሩ የሥራ እድል ፈጠራ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን የደቡብ ጎንደር ዞን ሥራና ሥልጠና መምሪያ ገልጿል። በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ተፈጥረዋል። ለወጣቶች የሥራ እድል እንዳይፈጠርም ችግር ኾኖ ቆይቷል።

የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ ምክትል ተወካይ ኀላፊ ወርቅነህ ባይሌ በ2016 በጀት ዓመት የሥራ እድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በክልሉ የተፈጠው የሰላም ችግር ግን ሥራውን ስኬታማ እንዳላደረገው ነው የተናገሩት። በዞኑ ለ119 ሺህ 13 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ ይዘው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል ተብለው በእቅድ ከተያዙት መካከል ለ6 ሺህ 744 ዜጎች ብቻ የሥራ እድል መፍጠራቸውንም አስታውቀዋል። ከሌሎች ጊዜያት አፈጻጸሞች እና ከታቀደው እቅድ አኳያ ዝቅተኛ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም 5 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ እቅዳቸውን ማሳካታቸውን ነው የተናገሩት።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ሥራቸውን በአግባቡ ለመፈጸም እንቅፋት ኾኖ መቆየቱንም አስታውቀዋል። የጸጥታ ስጋት የሥራ እድል ለመፍጠር አስቸጋሪ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ለ768 ኢንተርፕራይዞች የብድር ትሥሥር ለመፍጠር አቅደው ለ69 ኢንተርፕራይዞች ብቻ ትሥሥር መፍጠራቸውን ነው የገለጹት።

በዞኑ በሰላም እጦት ውስጥም ኾነው የተሻሉ ሥራዎችን የሠሩ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ወገዳ፣ ስማዳ፣ ላይ ጋይንት፣ ሊቦ ከምከም እና አዲስ ዘመን የተሻሉ የፈጸሙ መኾናቸውን ነው የገለጹት። በዞኑ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ያላደረጉ ከተማ አሥተዳደሮች እና ወረዳዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

ሥራ የተፈጠረላቸው ዜጎች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት ዘርፍ እና በንግድ መኾኑንም ተናግረዋል። የሥራ እና ሥልጠና ባለሙያዎች ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን ያነሱት አቶ ወርቅነህ የሰላም ሁኔታው መደበኛ ድጋፎች ለመስጠት እንቅፋት መኾኑን አመላክተዋል።

የሰላም ሁኔታው እንዲሻሻል ሁሉም መሥራት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችልም አንስተዋል። በቀሪ ወራት እቅዶቻቸውን ከልሰው የሥራ እድል ለመፍጠር እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

ችግሮችን በመቋቋም ለሥራ እድል ፈጠራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የጸጥታ ሁኔታው የብድር አመላለስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩንም ተናግረዋል። የሥራ እድል ፈላጊዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል። ሊመጣ የሚችለውን ጫና ታሳቢ በማድረግ ሁሉም መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሥራ እድል ፍላጎት ለማሟላት ሰላሙን ማጽናት ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ ኾነው ራሳቸውን እና ሀገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ወጣቶች የመፍትሔ አካል መኾን እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየልማት ድርጅቶች እያደገ በመጣው የኢንቨስትመንት አማራጭ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ።
Next articleጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ማስቀጠል እንደሚገባ ሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።