የልማት ድርጅቶች እያደገ በመጣው የኢንቨስትመንት አማራጭ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ።

48

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የልማት ድርጅቶች በሀገሪቱ እያደገ በመጣው የኢንቨስትመንት አማራጭ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ መንግሥት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን በአንድ በማሰባሰብ ወደ “ሆልዲንግ” ለማምጣት በሚያስችል ጉዳይ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በክልሉ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት እና አሠራር እንዲከተሉ ለማድረግ የአማራ ክልልን ኢንቨስትመንት ወደ አንድ ማምጣት ወይም “ሆልዲንግ” ማቋቋም አስፈልጓል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ባለፋት ዓመታት በክልሉ 13 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ የልማት ድርጅቶች በግንባታ፣ በንግድ እና በአገልግሎት ዘርፍ የመንግሥትን ክፍተት በመሙላት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።ድርጅቶቹ ከ8 ሺህ 500 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የልማት ድርጅቶች በተበታተነ መንገድ ያከናውኑት የነበረውን ተግባር በተማከለ መንገድ ለመምራት በኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ማቋቋም ማስፈለጉን ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ሆልዲንጉ ድርጅቶቹ ራሳቸውን በሰው ኃይል፣ በሃብት እና በቴክኖሎጂ አደራጅተው እና አቀናጅተው በሀገሪቱ እያደገ በመጣው የኢንቨስትመንት አማራጭ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ያደርጋል ነው ያሉት።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ በሆልድንግ መደራጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ የሥራ አደረጃጀት እንደኾነ ገልጸዋል። የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር አበባው ጌቴ በክልሉ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት እና አሠራር እንዲከተሉ ለማድረግ የአማራ ኢንቨስትመንት “ሆልዲንግ” ማቋቋም ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከ1990ዎቹ ጀምሮ የልማት ድርጅቶችን ሲያቋቁም በወቅቱ ደካማ የነበረውን የግል ዘርፍ የገበያ ክፍተት ለመሙላት ታስቦ እንደነበር ገልጸዋል። የልማት ድርጅቶችን በሆልዲንግ ማደራጀቱ የተማከለ አመራር፣ አደረጃጀት፣ አሠራር እና ቁጥጥር እንዲኖር ያደርጋል፤ የተበታተነውን ሃብት በተደራጀ መንገድ ለመምራት እና አቅጣጫ ለማመላከትም ያግዛል፤ በተማከለ መንገድ ለመደገፍ እና አቅማቸውን ለማሳደግ ይረዳል፤ የልማት ድርጅቶች እርስ በርሳቸው በኢኮኖሚና እና በቴክኖሎጅ እንዲደጋገፉ ያግዛል፤ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የብድር እና የውጭ ምንዛሬ ችግር ለማቃለል ያግዛል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ጥናትን መሠረት ባደረገ መንገድ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶችን ወደ አንድ የማደራጀት ሥራ ይሠራል። ችግር ያለባቸው እና ክልሉን ላላስፈላጊ ወጭ እየዳረጉ የሚገኙትን ደግሞ እንዲከስሙ ይደረጋል ወይንም ሌላ መፍትሔ ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ ሁለት ቀጠናዊ ውድድሮች የማዘጋጀት ኃላፊነት ተሰጣት።
Next article“የጸጥታ ሁኔታው የሥራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል” የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር