ለፉት ተከታታይ ዓመታት ባከናወኗቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ መኾናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ።

34

ባሕር ዳር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በቻግኒ ከተማ አሥተዳደር የ05 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጥላሁን ተሠራ እና አርሶ አደር አስማረች ባይህ የተፋሰስ ልማት መሥራት ከጀመሩ ወዲህ በአፈር ለምነት፣ በመኖ ልማት እና የአካባቢ ገጽታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማየታቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራት የሠሩትን የተፋሰስ ልማት ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ በሥነ-ህይወታዊ ዘዴ ማጠናከር እና ከንክኪ ነፃ ማድረግ ቀጣይ የቤት ሥራቸው እንደኾነም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) የ2016 በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በ310 ነባር እና አዲስ ተፋሰሶች ላይ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ ባለፉት ዓመታት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት እና የነበሩ ድክመቶችን በማረም ወጥነት ባለው መልኩ እየተፈጸመ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሩ በወቅታዊ ችግሮች ሳይወሰን ተፈጥሮን ተንከባክቦ ለትውልድ ለማስተላለፍ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነውም ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ 78 በመቶ የሚኾነው ሥራ መጠናቀቁን የገለጹት ኀላፊው ቀሪ ሥራዎችን እስከ የካቲት መጨረሻ ድረስ በማጠናቀቅ በዓመቱ የተያዘውን እቅድ ለመሸፈን በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ በይፋ በተጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ 310 ተፋሰሶች በነባር እና በአዲስ እየለሙ መኾናቸውን ከግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያዊ አንድነት የማይደራደር ትውልድ መገንባት አለብን” የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር
Next articleኢትዮጵያ ሁለት ቀጠናዊ ውድድሮች የማዘጋጀት ኃላፊነት ተሰጣት።