
ደብረ ታቦር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር “ዓድዋ ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የዓድዋ በዓል አከባበርን በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የተገኙ ወጣቶች ዓድዋ የኢትዮጵያ አንድነት መገለጫ በመኾኑ በድምቀት ልናከብረው ይገባል ብለዋል። ዓድዋ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድል እና ኩራት መኾኑንም ገጸዋል። በዓደዋ መነሻነት ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን ነው ያሉት። ዓድዋን ምንነት በሚገባ መረዳት እና የድል በዓሉን በተገቢው መንገድ መዘከር እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።
ዓድዋ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት አርማ መኾኑን ተናግረዋል። ዓደዋ ነፃነትን እና ጀግንነትን ብቻ ሳይኾን ሩህሩሕነትን፣ መቻቻልን እና መግባባትን እንደሚያስተምርም አንሰተዋል። ዓድዋ ታላቅን ማክበርን፣ ምርኮኛን እንዴት መያዝ እንደሚገባ፣ የመሪ እና የተመሪ መግባባትን የሚያስተምር መኾኑንም ገልጸዋል። መግባባት እና አንድነትን ማስቀደም እንደሚገባም ተናግረዋል።
ችግሮችን መፍታት የሚቻለው ሕዝብ እና መንግሥት አንድ ሲሆኑ መኾኑንም ተናግረዋል። የዓድዋን ታሪክ ኾነ ሌሎች የኢትዮጵያ ቀደምት ታሪኮችን ማሳወቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ትውልዱ ታሪኩን ሳያውቅ ታሪኩን ጠብቅ ማለት እንደማይቻልም አንስተዋል። በዓሉን ከንግግር ባለፈ በተግባር ማክበር ይገባል ነው ያሉት።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ተሳተፎ እና ንቅናቄ ቡድን መሪ ታዘብ ፋንታሁን ከምኒልክ እና ከጣይቱ ሀገር የመጠበቅ እና ሕዝብ የማኩራት ታሪክ መማር ይገባል ብለዋል።
ታሪኮቻችንን በሚገባ ማወቅ እና መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። አባቶች ሀገርን ለማቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። አባቶች በጦርነት ብቻ ሳይኾን በሌሎች ሥራዎች ለትውልድ የሚያኮራ ሥራ መሥራታቸውንም ገልጸዋል። ታሪክ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰለሞን የዓድዋን ድል በዓል ለማክበር የሚያስችሉ ውይይቶች በየክፍለ ከተሞች ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
ውይይቶቹ ከወጣቶቹ እና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በከተማዋ የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት መቆሙን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው በሐውልቱ ሥር የዓድዋ በዓል በድምቀት እንደሚከበርም አስታውቀዋል።
የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን አንድነት አስከብሮ ከመሄድ አንፃር ሰፊ ኀላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል። “አባቶቻችን ታሪካዊ ሀገር ነው ያስረከቡን” ያሉት አቶ ኃይለኢየሱስ ዳር ድንበሯ የተከበረች፣ ነፃነቷን የያዘች ሀገር አስረክበውናል፣ አባቶቻችን ሕይወታቸውን ሰውተው ያቆዩንን ሀገር በመጠበቅ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር ማስተላለፍ አለብን ብለዋል።
ከስሜታዊነት ወጥተን በምክንያታዊነት በማመን ኢትዮጵያዊነትን የሚያጸና ወጣት መገንባት ይገባል ነው ያሉት። ምክትል ከንቲባው “በኢትዮጵያዊ አንድነት የማይደራደር ትውልድ መገንባት አለብን” ሲሉ ነው የተናገሩት።
የአባቶቻችን እና የእናቶቻችን አደራ አለብን ካልን የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል። አደራውን ለመወጣት ደግሞ ሰላም ያሰፈልጋል ብለዋል።
ዓድዋን ስናከብር ለሰላም እና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። ከዓድዋ የተማርነውን አንድነት፣ ነፃነት፣ መልካምነት እና ርህራሄን ማስቀጠል አለብን ብለዋል። ሁልጊዜም ለሰላም መሥራት አለብን ያሉት ምክትል ከንቲባው ሰላም ከሌለ የታቀዱ ሥራዎች ሁሉ እንደማይሳኩ ነው የተናገሩት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!