
አዲስ አበባ: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ጋር ውይይት ማካሄድ ጀመረ። ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ዓ.ም ተቋቁሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በተለያዩ ምዕራፎች ከፋፍሎ ሲሠራ ቆይቷል።
እስካሁንም ባደረገው እንቅስቃሴ የተሳታፊዎች ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ደረጃ ላይ መድረሱን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናግረዋል። ከቀበሌ ጀምሮ በርካታ ውይይቶች መደረጋቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ አሁን ደግሞ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተወካዮች እና ምሁራን ጋር ውይይት ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እንደተደረገው ውይይት ሁሉ በግሉ ዘርፍ ከተሰማሩት የትምህርት ተቋማት እና ምሁራን ጋር የሚደረገው ውይይት ትልቅ ግብዓት የሚገኝበት ይኾናል ተብሎ ይታመንበታል ነው ያሉት።
የግል ከፍተኛ የትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ምሁራን በተሳትፎም ኾነ ለምክክር ኮሚሽኑ የሚያደርጉት ድጋፍ እና እገዛ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል። ተቋማቱ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ መኾናቸውም ተገልጿል ። ውይይቱ ዛሬ ሙሉቀን ተደርጎ የሚጠናቀቅ ሲሆን ሁሉም ኮሚሽነሮችን ጨምሮ አምሳደር ዶክተር ሽፈራው ሽጉጤ በውይይቱ ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!