ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ገለጸ።

37

ባሕርዳር: የካቲት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ገልጿል። የመምሪያ ኃላፊው ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) በተያዘው የምርት ዘመን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ተቅዶ 12 ሺህ 5 መቶ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በምርት ዘመኑ በመስኖ ስንዴ የለማው ማሳ ከተያዘው እቅድ እና ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ካለው የመልማት ፀጋ አንፃር ዝቅተኛ መኾኑንም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። ወቅታዊ የሰላም መደፍረስ፣ የማዳበሪያ አቅርቦት ማነስ እና ዘር በወቅቱ አለመቅረብ በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች ለተፈጠሩ ችግሮች ሳይበገሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ስንዴ በመስኖ እያለሙ ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው ሰብሉ በመልካም ቁመና ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳዳሩ ጓንጓ ወረዳ የአንጓይ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር አልጋነህ አካል እና አርሶ አደር አለሙ ገረመው በአካባቢያቸው ስንዴ ማምረት ከጀመሩ ከ15 ዓመታት በላይ እንደሆናቸው እና ከፍተኛ ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ የተፈጠረው የዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በስንዴ ምርታማነት ላይ ጫና የፈጠረባቸው ቢኾንም የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ችግሩን ለመቋቋም ጥረት ማድረጋቸውንም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በመስኖ ከለማው ስንዴ 400 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ምክር ቤት የተጓደሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን የሚያሟሉ አዳዲስ አባላትን ሰየመ።
Next articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ጋር ውይይት ማካሄድ ጀመረ።